ኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፉን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለማቀላጠፍ እየሰራች ነው...የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 3/2015 (ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፉን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለማቀላጠፍ  እየሰራች  መሆኑን   የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ። 

ይህ የተገለጸው በ9ኛው የህንድ-አፍሪካ አይ ሲ ቲ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ  ባለበት ወቅት ነው ። 

አውደ ርዕዩ በአይ ሲ ቲ  ዘርፍ የተሰማሩ የህንድ እና የአፍሪካ ሀገራት ካምፓኒዎችንና ባለሙያዎችን በማገናኘት ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁና በጋራ እንዲሰሩ ለማድረግ አላማን ሰንቋል ። 


 

ህንድ በቴሌኮሙኒኬሽን መጠቀሚያ መሳሪያዎች ምርትና እና አገልግሎት፣ በዲጂታል ጤና፣ ትምህርት፣ የመረጃ መረብ ደህንነት እና በሌሎች አይ ሲ ቲ ዘርፎችም በጋራ እየሰራች ትገኛለች። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ህንድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍም ያላቸው ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፉን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ የተቀላጠፈ ለማድረግ እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ አውደ ርዕዩ ሀገራቱ የጀመሩትን ምቹ የአይ ሲ ቲ ስነ-ምህዳር የመፍጠር ስራን ያጠናክራል ብለዋል።


 

በህንድ የቴሌኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር የጋራ ፀሃፊ ሱሚል ኩማር ቨርማ ህንድ የአይ ሲ ቲ አገልግሎትና የመጠመቀሚያ መሳሪያዎችን በማምረት እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ በዓለም ተወዳዳሪ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል። 

ዓውደ ርዕዩ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን ከህንድና ከኢትዮጵያ የተውጣጡ የተለያዩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መፍትሄዎች ለእይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም