ቀጥታ፡

የሥነ ምግባር ጥሰት በፈፀሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 3/2015 (ኢዜአ)፦የሥነ ምግባር ጥሰት በፈፀሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ።

ከተገልጋዮች በቀረበ ጥቆማ መሰረት ተጣርቶ በማስረጃ ጥፋተኛ መሆናቸው የተረጋገጡ 112 ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን ከተገልጋዮች በቀረበ ጥቆማ መሰረት 133 ጥቆማዎችን ተቀብሎ በ112 አመራርና ሰራተኞች ላይ ከጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ስንብት የሚደርስ አስተዳደርዊ እርምጃ መውሰዱንም አመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዲሲፕሊን ችግር በታየባቸው 1 ሺሕ 60 ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መወሰዱን ጠቅሶ በ288 ሠራተኞች ላይ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ719 ሠራተኞች ላይ የደመወዝ/ገንዘብ ቅጣት፣ በ39 ሠራተኞች ላይ ስንብት፣ በ9 ሠራተኞች ላይ ከቦታ ማንሳት እና በ11 ሠራተኞች ላይ ባደረገው ማጣራት ነጻ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን ለመቀበል ከተዘረጉ የ904 እና 905 ነጻ የጥሪ ማዕከላት በተጨማሪ ደንበኞች ቅሬታቸውን በቀላሉ ማቅረብ የሚችሉበት ዘመናዊ የሙስና ጥቆማ መቀበያ ሥርዓት ለመዘርጋት በሂደት ላይ መሆኑን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም