የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ አገር የማዳከም ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቶች ከሰራዊቱ ጎን ሊቆሙ ይገባል - የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ አገር የማዳከም ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቶች ከሰራዊቱ ጎን ሊቆሙ ይገባል - የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 3/2015(ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ አገር የማዳከም ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ወጣቶች ከሰራዊቱ ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ፡፡
መንግስት ልዩነቶች በሰላማዊ አማራጭ በውይይት እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሰራ ሲሆን፤ በዚህም በተለያዩ ክልሎች ነፍጥ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለስ መቻሉ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመቋቋም ጭምር ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ ይገኛል፡፡
ነገር ግን በቅርቡ በአማራ ክልል የታጠቁ ዘራፊ ኃይሎች መንገድ በመዝጋት፣የህዝብ ሃብቶችን በማውደምና በመዝረፍ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በተደራጀ አግባብ የኢትዮጵያ ህልውና የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ስም በሀሰት የማጠልሸት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ፈዲላ ቢያ እና አባንግ ኩሙዳን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያን ህልውና በጀግንነት በመጠበቅ የአገር አልኝታነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈዲላ ቢያ፤ ሰራዊቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ኩራት መሆኑን ተናግራለች፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ ማንነት ኢትዮጵያ መሆኗን ገልጻ፤ ሰራዊቱ አገር ለማፍረስ የተሞከሩ ጥቃቶችን በጀግንነት ያከሸፈ የአገር አርማ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ሌላኛዋ የፓርቲው ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት አባንግ ኩሙዳን በበኩሏ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የሚደረግ ትንኮሳ አገር የማፍረስ ውጥን መሆኑን ገልጻለች፡፡
በመሆኑም ወጣቶች እነዚህ ትንኮሳዎች አገርን ለማፍረስ የተቃጣ ጥቃት መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግራለች፡፡
ከዚህ አኳያ በአማራ ክልል ትጥቅ በማንገብ የሚንቀሳቀሰው ዘራፊ ቡድን መንገድ በመዝጋት ገበሬው የመኸር የእርሻ ወቅት ተረጋግቶ እንዳያከናውን እያደረገ መሆኑን ነው ፈዲላ ቢያ የተናገረችው፡፡
ወጣቶች የዚህ ዘራፊ ቡድን እንቅስቃሴ በዋናነት ክልሉን እንደሚያዳክም በመገንዘብ የጥፋት ቡድኑ ተባባሪ ሊሆኑ እንደማይገባ ገልጻለች፡፡
ከዚህ አኳያ ወጣቶች በሚሰሟቸው የሀሰት መረጃዎች ሊደናገሩ እንደማይገባ ገልጻ፤ ከየትኛውም አካል የሚመጣን መረጃ በምክንያታዊነት ማጣራት እንዳለባቸው ተናግራለች፡፡
አባንግ ኩሙዳን በበኩሏ የወጣቶች የልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚችሉት በዋናነት ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን መሆኑን ተናግራለች፡፡
በመሆኑም ወጣቶች ሰላም በማስጠበቅ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርባለች፡፡