በሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካኝነት ባለፉት ሦስት ወራት ከ53 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት እድል ተፈጥሯል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 3/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ በተደረገው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካኝነት ባለፉት ሦስት ወራት ከ53 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት እድል መፈጠሩን የሥና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

የሚኒስቴሩ አመራሮችን፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖችንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የሥልጠና እና የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ በቆይታው ተቋሙ ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ አቅዶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በትላንትናው ዕለትም በአመራር ጥበብና ስኬታማ የአሰራር ሂደቶች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደተናገሩት፤ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት በቴክኖሎጂ በመተጋዝ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ዲጂታል የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ወራትም በገበያ መረጃ ስርዓቱ አመካኝነት ከ53 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ አገር መሄዳቸውን ተናግረዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 105 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ለስራ መሰማራታቸውን ጠቁመው ይሄው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ከተዘረጋ ወዲህ የተለያዩ አገራት ፍላጎት እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ባለው 2 ሚሊዮን የስራ ፍላጎቶች ቀርበውልናል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ የሥራ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ዜጎችን በማወዳደር ወደ ሥራ የሚቀይሩበት የድጋፍ ማዕቀፍ መዘርጋቱን አብራረተዋል።

በስራ ፈጠራ ሀሳብ ውድደር አሸናፊ የሚሆኑ ዜጎች ከልማት ባንክ ጋር በመተባበር ስልጠና እና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ አግኝተው ወደ ሥራ የሚሰማሩበት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአጠቃላይ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በግብርና፣ አምራች፣ አገልግሎትና መሰል መስኮች ለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም