ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ፓኪስታን በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ምክክር ዛሬ አድርገዋል።

ውይይቱን ያደረጉት በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከርና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱላሂ ሁሴን የተመራ ልዑካን ቡድን እንዲሁም የፓኪስታን ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ባሴር አቻክዛይና ሌሎች የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ናቸው።


 

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በኢትዮጵያ ያለውን የጤና አጠባበቅ ስርዓት እና የሕክምና ትምህርት ስልጠና ላይ ያተኮረ ገለጻ አድርገዋል።

በጤና አጠባበቅ ዘርፍ በሁለቱ አገራት መካከል ተቋማዊ ትስስር መፍጠር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በውይይቱ ሁለቱ አገራት በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ተስማምተዋል።

የልዑካን ቡድኑ የፓኪስታን የሕክምና ሳይንስ ተቋምን የጎበኘ ሲሆን በሕክምናው ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት ማድረጉን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም