ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል አስታወቀ

ሐረር ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል በተያዘው 2016 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትና በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመላው ኢትዮጵያውያን ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት እየተገነባ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ የብልፅግና ጉዟችንን የሚያፋጥን በሕዳሴ ምዕራፍ ውስጥ የሚደምቅ የሀገራችን ብርሃን ነው ብለዋል።

የክልሉ ህዝብም ባለፉት 12 ዓመታት በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለግድቡ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ በክልሉ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውሰዋል።

ገንዘቡ የተሰበሰበው በቦንድ ግዢና በስጦታ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሰበሰበውም በዘመኑ በእቅድ ከተያዘው በላይ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ድጋፉ በክልሉ ከሚገኙ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከወጣቶችና ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ የሚገኙ መላው ህብረተሰብን በማሳተፍ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ሄኖክ አስታውቀዋል።

በክልሉ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የተያዘው እቅድ ስኬታማ እንዲሆን በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች የውይይት እና የህዝብ ንቅናቄ የመፍጠር ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት እያከናወነ የሚገኘውን የድጋፍ ስራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አቶ ሄኖክ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም