ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገለጹ።

አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ከሕንድ የንግድ፣ ዘላቂ ልማት እና የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አብሂናቭ ባይላን ጋር በኢትዮጵያ ባሉ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን አምባሳደር ደመቀ ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም መንግስት ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶች መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች እና የንግድ አመቺነት አሰራሮች ላይ ማሻሻያ ማድረጓን አመልክተዋል።

የሕንድ የንግድ፣ ዘላቂ ልማት እና የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አብሂናቭ ባይላን በበኩላቸው ምክር ቤቱ ኒው ዴልሂ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዚህም በሕንድ የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች የሚያስተዋውቁ ሴሚናሮችን እንደሚያዘጋጅ መግለጻቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1950 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም