ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ትሰራለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ትሰራለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር በተለያዩ የትብብር መስኮች ያሏትን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩበት 60ኛ ዓመት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በባህል፣ በኢንቨስትመንትና በመሰል የጋራ ጉዳዮች ላይ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን ቀዳሚ የልማት አጋር አድርጋ መምረጧ እንደሚያስመሰግናት ገልጸው፤ የሁለቱ አገራት ረዥም ታሪክ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።
በዛሬው ውይይታቸውም አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መምከራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በጋራ መልማት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ተመራጭ የልማትና የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ሪፐብሊክ ሰላምና ነፃነት መስዋዕትነት መክፈላቸውን አንረሳውም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ያላትን ወዳጅነት ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረግነው ውይይት በሰው ኃይል ልማት፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት መስኮች ትብብራችንን ለማጠናከር ስምምነት ደርሰናል ብለዋል።
በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት የኮሪያ-አፍሪካ ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት ትብብር ለማጠናከር እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።
አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ-ልማት ግንባታና በሌሎች ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገውን ትብብር ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።