በ2016 በጀት ዓመት 100 አዳዲስ የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በ2016 በጀት ዓመት 100 አዳዲስ የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ በ2016 በጀት ዓመት 100 አዳዲስ የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ።
በተጨማሪም በ2016 በጀት ዓመት ገቢውን ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ገልጿል።
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ፤ የተቋሙን የ2015 የሥራ አፈጻጸምና የ2016 ዕቅድ በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት 13 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 582 አገልግሎት መስጫ ማዕከላትና 6 ሺህ 448 ሳተላይት መለያዎችን በማዋቀር ለደምበኞች አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል።
በ2015 በጀት ዓመት 125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ በማድረግ የዕቅዱን 78 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ነው የተናገሩት።
በቀጣይም በ2016 በጀት ዓመት 600 ሺህ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደምበኞችን በማፍራት ተደራሽነቱን ይበልጥ ማሳደግ ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
ተቋሙ በ2015 በጀት ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዳዲስ የኤሌክትሪክ ማስቀጠያና ከንብረት ማስወገድ 35 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ዕቅዱን 94 በመቶ ማሳካት ችሏል ብለዋል።
በቀጣይም በ2016 በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 8 ቢለዮን ብር፣ ከልዩ ልዩ የሽያጭና መሰል ገቢዎች 260 ሚሊዮን ብር፣ ከአዳዲስ ኃይል ማስቀጠያ 11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም አክለዋል።
በአጠቃላይ በ2016 በጀት ዓመት ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልፀዋል።
ተቋሙ ዕቅዱን በሚፈለገው መልኩ ለማሳካት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ንረት ተግዳሮት እንደሆነበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅና በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆትና ውድመቶች የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውንም እንዲሁ።