በኩታ ገጠም በቆሎ ማልማት መጀመራችን ምርትና ምርታማነታችን እንዲሻሻል አድርጓል - የሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በኩታ ገጠም በቆሎ ማልማት መጀመራችን ምርትና ምርታማነታችን እንዲሻሻል አድርጓል - የሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 2/2015 (ኢዜአ)፡- በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በቆሎ ማልማት መጀመራችን ምርትና ምርታማነታችን እንዲሻሻል አድርጓል ሲሉ የሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዲያ ዞን አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የበቆሎ ምርት ላይ በመሰማራት ውጤታማ መሆን መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የበልግ ወቅት "ሊሙ" የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘርን በኩታ ገጠም ማልማት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የተሻለ ምርት አንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት አርሶ አደር መካከል ከድር ዋዎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የግብርና ግብዓትን በአግባቡ ለመጠቀም እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት፡፡
በዚህም ምርትና ምርታማነታቸው መሻሻሉን ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር የበቆሎ ማሳ እስከ 40 ኩንታል ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ በዘንድሮው በልግ ወቅት ካለሙት በቆሎ ሰብል የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ አብራርተዋል፡፡
ይህም ከራሳቸው ባለፈ ለገበያ የሚውል ምርት እንዲያመርቱ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴን በማስፋት ረገድ አርሶ አደሩ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ዋባ መሴ ማሴቦ ናቸው፡፡
የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ተረፈ በተያዘው የበልግ ወቅት በሀዲያ ዞን ከ81 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ምርቶች መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 11 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዘር ከተሸፈነው መሬትም 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሃላፊው ገለጻ፤ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በዞኑ ያለውን ምርትና ምርታማነት እያሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉን በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሃዲያ ዞን በቆሎን በኩታ ገጠም በማምረት ከዚህ ቀደም በአንድ ሄክታር በአማካይ ይገኝ የነበረውን 45 ኩንታል ምርት ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡