በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት ሆኖ የቆየው የጤና አውደ ርዕይ የዘርፉን ቴክኖሎጂዎች ከማስተዋወቅ ባሻገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጠናከር እድል የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት ሆኖ የቆየው የጤና አውደ ርዕይ የዘርፉን ቴክኖሎጂዎች ከማስተዋወቅ ባሻገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጠናከር እድል የፈጠረ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት ሆኖ የቆየው የጤና አውደ ርዕይ በዘርፉ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ አቅም ከማስተዋወቅ ባሻገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲጠናከር እድል የፈጠረ እንደነበር የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ትብብር በሳይንስ ሙዚየም ለተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ ስኬታማነት አስተዋጽዖ ለነበራቸው ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና መርኃ-ግብር ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ አውደ-ርዕዩ አቅሞችን በማቀናጀት የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች የታዩበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በአውደ-ርዕዩ ላይ በምርምር የተደገፉ ሀገር በቀል የሕክምና እውቀቶች እና ዘመኑ የደረሰበትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) የሕክምና አገልግሎት ለዕይታ መቅረቡን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ውጤታማ ሰብዓዊ ነፃ የሕክምና ምርመራና የምክር አገልግሎት፣ የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ የተደረገበት እና የዓይን ብሌን ልገሳ ቃል የተገባበት እንደነበርም አንስተዋል።
በተመረጡ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይም ለጤና ፖሊሲ እና ፕሮግራም ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦች የተገኙባቸው የተለያዩ ውጤታማ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።
አውደ-ርዕዩን ከ210 ሺህ በላይ ዜጎች መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በኤግዚቢሽኑም ለ6 ሺህ 858 ሰዎች የደም ግፊት ምርመራ አገልግሎት በመስጠት የግፊት መጠናቸው ጭማሪ ያሳዩ ለ1ሺህ 858 ሰዎች የሕክምና እና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 160 ዜጎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን በመጠቆም፤ 220 ዩኒት ደም ልገሳ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይም በጤና አውደ-ርዕዩ ለ7ሺህ 955 ሰዎች ነፃ የጤና ምርመራ እና የምክር አገልግሎት በመስጠት ስኬታማ ኤግዚቢሽን መካሄዱን አንስተዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ ሌሎች ተባባሪ አካላትና የልማት አጋሮች ለጤና አውደ-ርዕዩ ስኬት ለነበራቸው ጉልህ አስተዋጽዖም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ምስጋና አቅርበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሐይ ጳውሎስ፤ በአውደ-ርዕዩ የጤና ሥርዓቱ የደረሰበት ደረጃ የታየበትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተነሳሽነት የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዜጎችን የሕክምና ፍላጎት ምላሽ መስጠት የሚያስችል በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የማይበገር የጤና ሥርዓት በመገንባት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
የመንግሥትና የግል ትብብርን በማጎልበት በጤና አውደ-ርዕዩ ላይ የታዩ ስኬታማ ቅንጅታዊ አሠራርና ትብብሮችን ለቀጣይ የጤና ሥርዓት መሻሻል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸውም እንዲሁ።
የግል ጤና ተቋማት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ግርማ አባቢ፤ አውደ-ርዕዩ የመንግሥትና የግል አጋርነት ውጤታማነትን ወደተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረበት እንደሆነ ገልፀዋል።
ለዕይታ የቀረቡት ምርትና አገልግሎቶችም የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ የጤና ሥርዓት የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል።
"የመጪው ትውልድ ጤና" በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን ብሔራዊ የጤና አውደ-ርዕይ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።
በጤና አውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡ ምርትና አገልግሎቶችን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲዎች እና የጤናው ዘርፍ የምርምር ተቋማትና ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጎብኝቷል።