ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ በ2015 በጀት ዓመት 125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በተጨማሪም አገልግሎቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 35 ቢሊዮን 458 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ገቢውን ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ አቅድ መያዙን ገልጿል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የተቋሙን የ2015 የስራ አፈፃጻም እና የ2016 እቅድ በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት 13 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 582 አገልግሎት መስጫ ማእከላት እና 6 ሺህ 448 ሳተላይት መለያዎችን በማዋቀር ለደምበኞች አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ በማድረግ የእቅዱን 78 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡

ተቋሙ ገቢ በማሳደግ በኩል በኢነርጂ ሽያጭና በልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች 37 ቢሊዮን 750 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቅዶ 35 ቢሊዮን 458 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የእቅዱን 94 በመቶ ማሳካቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ገቢውን ወደ 45 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም 600 ሺህ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ደምበኞችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ነው ያሉት፡፡

100 አዳዲስ የገጠር ከተሞችንም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግና በሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ በ2016 በጀት ዓመት ትኩረት የተሰጣቸው ስራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም