በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተገኝቷል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተገኝቷል- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 2/2015 (ኢዜአ) ፦ በ2015 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መገኘቱን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
269 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸሙን አስገምግሟል።
ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ማዕድን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በስፋት የተሳተፉባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች መሆናቸው ተገልጿል።
በበጀት አመቱ በማኑፋክቸሪንግ 71 እና በአገልግሎት 22 ፕሮጀክቶች እንዲሁም በግብርና አንድ ፕሮጀክት ስራ መጀመሩን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ገልጸዋል።
269 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን በመጠቆም።
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኤክስፖርት 148 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንና በበጀት አመቱ ለ67 ሺህ ገደማ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አመልክተዋል።
ሶስት የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግንባታ ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በሚያዚያ/2015 በተካሄደው ‘ኢንቨስት ኢትዮጵያ ፎረም’ ወቅት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ካላቸዉ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈረሙን ነው ኮሚሽነሯ ያወሱት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነመራ ገበዬሁ ኮሚሽኑ የሚወዳደረው ከሌሎች አገራዊ ተቋማት ጋር ሳይሆን ከሌሎች አገራት መሰል ተቋማት ጋር መሆኑን ገልጸው ለዚህም ራሱን ማብቃት ላይ በትኩረት መስራት እንዲሁም አደረጃጀቱንና አገልግሎቱን ማዘመን አለበት ብለዋል።
ከተቋማትና ከክልሎች ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ይህም የቢዝነስ ስራ አመቺነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
በግምገማው ላይ የሶስት ዓመቱ የመካከለኛ ዘመን የመንግስት የልማትና የኢንቨስትመንት እቅድ ቀርቦ ውይይት እንደተካሄደበት ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።