መንግስት 13 ቢሊዮን ብር መድቦ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አድርጓል -የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት 13 ቢሊዮን ብር መድቦ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አድርጓል -የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
ሀዋሳ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ) ፡- በሀገሪቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባጋጠሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግሥት 13 ቢሊዮን ብር መድቦ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኮሚሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የሁሉም ክልሎች የጋራ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች፣ በአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ በዝግጁነትና ምላሽ፣ በመልሶ ማቋቋምና በሃብት ማሰባሰብ በኩል አመርቂ ተግባራት አከናውኗል።
በተለይ ሰው ሰራሽና የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸውን ችግሮች በጋራ ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን ገልጸዋል።
"ከዚህ አንፃር የቅድሚያ ቅድሚያ፣ ቅድሚያና ትኩረት የሚሹ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በጥናት ተለይተው የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል" ብለዋል።
በዋናነት ድርቁ ወደ ረሀብ እንዳይቀየር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን አመላክተዋል።
ለዚህና ለሌሎች ችግሮች ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በመደበው 13 ቢሊዮን ብር የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ስኬታማ ስራ ማከናወን መቻሉን አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ ለዘርፈ-ብዙ አደጋ የተጠናከረ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ተግባራት ሀብት በማሰባሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል ግብ ተይዞ መከናወኑን ኮሚሽነሩ ጨምረው ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በ2015 በጀት አመት በሃገሪቱ በአጠቃላይ በተለያዩ ምክንያቶች ለደረሰ አደጋ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ በመንግስትና በአጋር አካላት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምግብ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ከ4 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስና አልባሳት እንዲሁም ለ131 ሺህ ወገኖች ለመኖሪያ ቤት ጥገና አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።
ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱን ታሳቢ ያደረገ የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲን የመከለስ ስራ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
"ይህም በአብዛኛው በውጭ ድጋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ሚዛኑን እንዲጠብቅና በሀገር በቀል አቅም ሰብአዊ ድጋፍን የመሸፈን ግብ እንዲሳካ ምቹ መደላደል ይፈጥራል" ብለዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ በአይነቱ ልዩ የሆነ የኢትዮጵያ የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ተቋም ማደራጀት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ሚኒስቴር ቀርቧል።
ከመድርኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር መልቻ ሎቻ በሰጡት አስተያየት በክልሉ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን በሰብአዊ እርዳታ ለመድረስ የተለያዩ አማራጮችን በመንደፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የገዳ ሥርዓት አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ሥርዓት በሆነው ”ቡሳ ጎኖፋ” አማካኝነት በድርቅና በሌሎች ሳቢያ ለችግር ለሚጋለጡ ወገኖች ድጋፍ የሚውል በዘላቂነት ሀብት ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ በኩል በክልሉ ለ17 ሚሊዮን ህብረተሰብ ግንዛቤ በመፈጠር 12 ሚሊዮን የቡሳ ጎኖፋ አባል ማፍራት መቻሉን አስታውቀዋል።
ከአባላቱ ላይ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ መዋጮ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ለተጎጅዎች መድረስ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የደቡብ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አሸብር ደምሴ በበኩላቸው በክልሉ በድርቅ ምክንያት ለአስቸኳይ እርዳታ ለተጋለጡ ወገኖች ሰብአዊ አቅርቦቱ የተሟላ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
በተለይ የድጋፍ አድራጊዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ተጨማሪ የሃብት ግኝትን ማሰባሰብ የሚያስችልና ተናባቢና ቅንጅታዊ የሆነ አሠራር እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
"በዚህ በኩል በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በድርቅ ሳቢያ ለችግር ከተጋለጡ የህበረተሰብ ክፍሎች ውስጥ 900 ሺህ የሚሆኑት የሴፍቲኔት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል" ብለዋል።
ቀሪዎቹ ተረጂዎች ደግሞ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም በየደረጃው በሚገኘው መዋቅርና ህብረተሰብ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ ከሁለት ከተማ አስተዳደሮችና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።