ለአንድ ወር የቆየውን ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ከ210 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል-ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ለአንድ ወር የቆየውን ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ከ210 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል-ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 01/2015 (ኢዜአ)፦ በሳይንስ ሙዚየም ለአንድ ወር የቆየውን ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ከ210 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደጎበኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ይህን ያሉት በሳይንስ ሙዚየም ለአንድ ወር በቆየው የጤና አውደ-ርዕይ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት እየተካሄደ ባለው የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ ጳውሎስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የጤና ስርዓት ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
የጤናው ዘርፍ የደረሰበትን ምርትና አገልግሎት ዜጎች እንዲመለከቱት በማሰብ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በይፋ ተከፍቶ ለአንድ ወር በቆየው የጤና አውደ ርዕይ፤ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያከናወነቻቸው የልማት ሥራዎች ለዕይታ መቅረባቸውን አስታውሰዋል።
"የመጪው ትውልድ ጤና" በሚል መሪ ሃሳብ ለህዝብ ዕይታ ክፍት ሆኖ የቆየው ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ውጤትም የታየበት እንደሆነ አክለዋል።
በዚህም አውደ ርዕዩ ለአንድ ወር በነበረው ቆይታ፤ ከ210 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሳይንስ ሙዚየም ተገኝተው እንደተመለከቱት ተናግረዋል።
በኤግዚቢሽኑም 6 ሺህ 858 ሰዎች የደም ግፊት ምርመራ ማድረጋቸውን፣ 450 ሰዎች የዐይን ጤና ምርመራ፣ 220 ዩኒት ደም ልገሳ የተደረገበት፣ ለ300 ሰዎች የቆዳ ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል።
ለጤና አውደ-ርዕዩ ዝግጅት በርካታ ተባባሪ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ለስኬቱም አስተዋጽኦ ለነበራቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
አውደ-ርዕዩ የፌደራልና የክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የጤናው ዘርፍ የምርምር ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጎብኝቷል።