በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት አባል ሀገራት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት አባል ሀገራት ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 01/2015 (ኢዜአ) ፦በቀጣናው የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት አባል ሀገራት ትብብራቸውን በማጠናከር የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ፡፡
ለየምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር "የፖሊስን አቅም በማጎልበት የቀጣናው ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሰንዳፋ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የ10 ቀን ስልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡
በስልጠናው ላይ ከዘጠኝ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ አባል ሀገራት የተውጣጡ 23 ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡
የጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ ዘርፍ ኃላፊ ኮሚሽነር አሊ ሰይድ ባካር እንዳሉት፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማርገብ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡
ለዚህ ደግሞ የፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን ዝግጁነትና አቅም መገንባት ይጠበቅበናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና፤ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በብቃት ለመወጣት አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም አባል ሀገራት የቀጣናውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅና የንጹሃንን ደህንነት ለማረጋገጥ የተሟላ ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ የቀጣናው ሀገራት የጋራ የፖሊስ አቅም ግንባታ በምሥራቅ አፍሪካ በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ላይ የጋራ ስምሪት መውሰድ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ፖሊስ በተሰማራበት ቀጣና የህዝብና የተቋማትን ሰላምና ደህንነትን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ባሟላ ሁኔታ ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን፤ ከኢንተር ፖል፣ አፍሪ ፖል እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ የፖሊሶች ህብረት ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
በተለይ እንደ ሽብርተኝነትና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ያሉ የተደራጁና ደንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ትብብር እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የዕቅድ፣ ስልጠናና ግምገማ ዘርፍ አስተባባሪ ሪቼል ሙንጌ ከእያንዳንዱ አባል ሀገራት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ሌሎችን በማሰልጠን ለተልዕኮ ዝግጁ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በዚህ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያሉ በቂ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ ተቋማት፣ ባለሙያዎችና የሥልጠና መሳሪያዎች ያሏት ሀገር መሆኗን አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ጋር በቅንጅት በመስራት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሏን ሚና እየተወጣች መሆኑንም እንዲሁ።