ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ምክክሩን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል - ምሁራን  

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ) ፦ መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ምክክሩን በተመለከተ ትክክለኛና ተከታታይ ዘገባዎችን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ሲሉ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። 

በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአገሪቱ በዋና ዋና ጉዳዮች የሚስተዋለውን ልዩነቶች በመፍታት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዓላማ አድርጓል።

ይህንንም ተከትሎ ኮሚሽኑ አሁን ላይ የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮውን እንዲያሳካ በተለይ ከሚዲያ አካላት ምን ይጠበቃል? ሲል የዘርፉ ምሁራንን ጠይቋል።

ምሁራኑም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ሕዝቡ ስለ አገራዊ ምክክሩ ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበትና ተሳትፎውን ለማረጋገጥ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አብዱልአዚዝ ዲኖ፤ ምክክሩ በውጤት እንዲጠናቀቅ የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም ከሚዲያ አካላት ግን ብዙ ይጠበቃል ብለዋል። 

በመሆኑም የሚዲያ አካላት ስለ አገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ትክክለኛና ተከታታይነት ያላቸው ዘገባዎችን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

"ሚዲያ መወያያም ማወያያም መድረክ በመሆኑ የተመረጡ አጀንዳዎችን በመቅረጽ በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸውን ሰዎች እየጋበዙ ስለ አገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት ማወያየት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

ይህን በማድረግ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።


 

መደበኛ ሚዲያዎች አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን አስፈላጊነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ዲጂታል ሚዲያውን በስፋት መጠቀም አለባቸው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ዶክተር ኤሊያስ ወርቁ ናቸው። 

የዲጂታል ሚዲያውን በመጠቀም ስለ አገራዊ ምክክሩ ሕብረተሰቡን ማስገንዘብና በሂደቱም ንቁ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። 

አገራዊ ምክክሩ አጀንዳ በማድረግ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም