ቀጥታ፡

የመዲናዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 
“ተግዳሮቶች ያልበገረው ለውጥ” በሚል ለሶስት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የከተማ አስተዳደሩ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።

“በበጀት ዓመቱ ውጤት ያገኘንባቸው ስራዎቻችን የምንረካባቸው ሳይሆኑ የጀመርናቸውን በማስፋት የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል፣ ለኑሮ ምቹ፣ ተወዳዳሪና የኢትዮጵያ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማ ለመገንባት ይበልጥ ተነሳሽነት የፈጠርንባቸው ነበሩ” ብለዋል ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።

የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች በማጠናከር፣ ፍትሐዊ አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በማስተካከልና አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ረገድ መሻሻል ቢኖርም በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበት አመልክተዋል። 


 

“ለውጡ ሕዝብ ፈልጎ ያመጣውና የሚደግፈው በመሆኑ ተግዳሮት የሚያደናቅፈው አልሆነም” ሲሉ ገልጸዋል። 

“የሕዝብን እምነት ጉልበት በማድረግ፣ የአመራሩን አቅም በማጎልበት እና ለሕዝብ የሚወግኑ ተቋማትን እየገነባን የነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

የከተማዋን ሰላም ለማስከበር ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በመሆን ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡባት ከተማ እንድትሆን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

“ለፀረ ሰላም ኃይሎች በእብሪት የሚመጣ ስልጣን እንደሌለ አሁንም ከተማችን ጥሩ ማሳያ ትሆናለች” ብለዋል።

“ጽንፈኝነትና አክራሪነት በተግባር በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የተሸነፈባት፣ ሰላሟ በዘላቂነት በሕዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠላትና ለሁሉም የምትመች፣ እንደ ስምዋ የተዋበች አዲስ አበባን እውን ለማድረግ በትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን” ነው ያሉት ከንቲባዋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም