ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ስምንት አዳዲስ የመንገደኛ አውሮፕላኖችን በጥቂት ወራት ውስጥ ይረከባል  - አቶ መስፍን ጣሰው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ስምንት አዳዲስ የመንገደኛ አውሮፕላኖችን በጥቂት ወራት ውስጥ ይረከባል - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ካዘዛቸው 26 አውሮፕላኖች ውስጥ ስምንቱን በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ ተጨማሪ 26 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ጋር ድርድር እያደረገ ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን ለማስገባት ድርድር የሚያደርገው ከቦይንግና ከኤርባስ ከተሰኙ ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከተገዘት አውሮፕላኖች መካከል አየር መንገዱ ስምንት የመንገደኛ አውሮፕላኖች በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብ ነው የገለጹት።

ቀሪዎቹ የመንገደኞች አውሮፕላኖች በቀጣይ ጊዜያት እንደሚገቡ ገልጸው አየር መንገዱ ሌሎች ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም አየር መንገዱ በሰኔ ወር ከቦይንግ ኩባንያ ሊረከባቸው ግዥ የፈጸመባቸው ሁለት አውሮፕላኖችም በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወራት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አየር መንገዱ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የመዳረሻ ሥፍራዎችን ከማስፋት አኳያ በቀጣይ ጥቅምና ህዳር ስድስት የበረራ መዳረሻዎች እንደሚጨምር ተናግረዋል።

እነዚህ የበረራ መዳረሻዎች በአብዛኛው የአውሮፓ አገራትን እንዲሁም አንድ አፍሪካ አገርን ትኩረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም።

ስፔን ማድሪድ፣ እንግሊዝ ለንደን-ጋትዊክ፣ ኔዘርላንስ አምስተርዳም፣ ቬትናም ሃኖይና ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጓይ የአየር መንገዱ አዳዲስ መዳረሻዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢውን በ22 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የአውሮፕላን ቁጥር መጨመርና ከበረራ መዳረሻውን ማስፋት በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ማስፋፊና የደንበኞች አገልግሎት የማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱን በሌሎችም በርካታ ዘርፎች የሪፎርም ሥራ በማጠናከር የታቀደውን እድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ መስፍን አብራርተዋል።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት 145 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን 134 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም