የወተት ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ የሌማት ትሩፋት ዕቅዱ ከግብ እንዲደርስ በትኩረት ይሰራል - ዶክተር ግርማ አመንቴ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ)፦ የወተት ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ የሌማት ትሩፋት ዕቅዱ ከግብ እንዲደርስ ለክልሎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ፡፡ 

የግብርና ሚኒስቴር የወተት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ለኦሮሚያ፣ ለአማራ፣ ለደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንዲሁም ለሲዳማ ክልሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ድጋፉንም የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ለክልል ግብርና እና እንስሳት ሃብት ቢሮ ሃላፊዎች አስረክበዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የወተት ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ የሌማት ትሩፋትን ከግብ እንዲደርስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡ 

ከዓለም ባንክ በድጋፍ የተገኙት እነዚህ ተሸከርካሪዎች በክልሎች ያለው የወተት ሃብት ወደ ተጠቃሚው እንዲሁም ወደ ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የተሸከርካሪ ድጋፉን ያገኙት አራቱ ክልሎችም ወተት በስፋት የሚመረትባቸው መሆናቸውን ጠቁመው ፤ ድጋፉ ወተትን ከሚያቀናብሩ ፋብሪካዎች ጋር የጀመሩትን ትስስር ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው ተሸከርካሪዎቹ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከ33 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደረገባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ዛሬ በድጋፍ የተሰጡ ተሽከርካሪዎች እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ 10 ሺህ ሊትር የወተት ምርቶችን በማሰባሰብ ወደተፈለገበት ቦታ ማድረስ እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ ድጋፉ በክልሉ የተጀመረው የወተት ሃብት ልማት ስኬታማ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል የሚመረተው ከፍተኛ ወተት ምርት ለብክነት እንዳይዳረግ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆንባ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ስኬታማ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ ድጋፉ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ 

ድጋፉ በክልሉ በወተት ሃብት ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ህብረት ስራ ማህበራት፣ ኢንቨስተሮች እንዲሁም ዩኒየኖችን ከመደገፍ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡      

ባለፈው በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ሊትር ወተት መመረቱ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ አማካይ ዓመታዊ ምርትን 11 ቢሊዮን ሊትር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም