በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት የቀረበ 331ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው- ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት የቀረበ 331ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ ነው- ቢሮው
መቀሌ ፤ ሐምሌ 30 /2015 (ኢዜአ )፡- በትግራይ ክልል ለመኽር ወቅት ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 331 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በፌደራል መንግስት በኩል ቀርቦ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።
የዝናብ ውሀ በመያዝና የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየተጉ መሆናቸውን በክልሉ የእንደርታ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የገጠር የፋይናንስና ግዢ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ገብረስላሴ ኪዳኑ ለኢዜአ እንደገለፁት ለመኽር ወቅት ለምርት ማሳደጊያነት የሚያገለግል 331 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በፌደራል መንግስት በኩል ቀርቦ ከ70 በላይ ለሚሆኑ ወረዳዎች ተከፋፍሏል።
አሁን ላይ የአፈር ማዳበርያው በወረዳዎቹ በሚገኙት የህብረት ሥራ ማህበር ዩኔየኖች አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ እንደርታ ወረዳ የሻፋት ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ወልዱ ካህሳይ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው እየተስተዋለ ያለው የክረምቱን ዝናብ መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የግብርና ስራቸውን እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የሚጥለውን ዝናብ በማቆር የማሳቸውን እርጥበት በመጠበቅ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ የእርሻ ስራቸውን እያካሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የማሳ ውስጥ እርከን በመስራትና ውሀ በመቋጠር እንዲሁም የአፈር ማዳበርያ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ እየተጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ትውረስ መኮንን ናቸው።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር አያሌው ደስታ በበኩላቸው "በወረዳው ከሚገኝ የህብረት ሥራ ማህበር ዩኔየን የገዛሁትን አንድ ኩንታል የአፈር ማዳበርያ በመጠቀምና የማሳየን አርጥበት በመጠበቅ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየተጋሁ ነኝ” ብለዋል።