የብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታ ለበርካታ እድሎች በር የሚከፍት መልካም ጅማሮ ነው - አምባሳደር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታ ለበርካታ እድሎች በር የሚከፍት መልካም ጅማሮ ነው - አምባሳደር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 1/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሜሪካ ቆይታ በቀጣይ ለበርካታ እድሎች በር የሚከፍት መልካም ጅማሮ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
ዋልያዎቹ በአሜሪካ ያደረጓቸውን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች አሸንፈዋል።
አምባሳደር ስለሺ በቀለ የወዳጅነት ጨዎታዎችን ለማካሄድ ወደ አሜሪካ ለመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የእንኳን ደህና መጣችሁ የእራት ግብዣ አድርገዋል።
ቡድኑ በወዳጅነት ጨዋታዎቹ የጉያናን ብሔራዊ ቡድንን 2 ለ 0 እንዲሁም ሎደን ዩናይትድን 4 ለ 2 አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ በአሜሪካ ያደረገው ጉዞ የመጀመሪያ እንደ መሆኑ መጠን የተገኘው ስኬት በርካታ እድሎችን የሚከፍት እና ወደፊት ብሔራዊ ቡድኑ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እጅግ የሚያበረታታ ጅማሮ ነው ብለዋል አምባሳደር ስለሺ።
ቡድኑ በአሜሪካ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርግ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደር ስለሺ 2016 ለብሔራዊ ቡድኑ የውጤትና ስኬት እንዲሆን በጎ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በኤምባሲው በኩል ለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና ድጋፍ ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታውን አጠናቆ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።