የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች በዛሬው እለት እውቅና ሰጥቷል።
የእውቅና መርሃ-ግብሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በዋናነት የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት ላይ ዓላማ ያደረገ ሲሆን፤ በስምንት ዘርፍ ለታጩ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል።
በዚህም ከፍተኛ ሽያጭ ላስመዘገቡ፣ ታማኝነታቸውን በተግባር ላሳዩ እንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ላይ የተሻለ ስራ ላከናወኑ ድርጅቶች ነው እውቅናው የተሰጠው፡፡
የቱሪዝም ሚንስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገር ባለፈ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
በአብዛኛው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ምርጫቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለቱሪዝም እድገት በጎ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት እውቅና የተበረከተላቸው የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኝ ድርጅቶችም ለዘርፉ እድገት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው አንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጉዞዎችን በማበረታታት እንዲሁም በማስተዋወቅ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርትን ከማቀላጠፍ ባሻገር ለቱሪዝም እድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍን ማሳደግ አገራዊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ በአየር መንገዱ እና በጉዞ ወኪሎች መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር አለበት ብለዋል።
አየር መንገዱም ግንኙነቱን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
እውቅና ከተበረከተላቸው መካከል የኤር ሊንክ የጉዞ ወኪል ስራ አስኪያጅ የማነ ብስራት በተበረከተላቸው እውቅና የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በቀጣይም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የሴፍ ዌይ ትራቭል ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ስራ አስኪያጅ ኢማን ዱሪ ለበርካታ ዓመታት በዘርፉ ያካበቱትን ልምድ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የውጭ አገራት ዜጎች ቁጥር ከፍ እንዲል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የተሰጠው እውቅና ላለቀ ስራ እንደሚያነሳሳ የተናገሩት ደግሞ የቪንቴጅ ትራቭል ሰርቪስ ስራ አስኪያጅ አቡበከር መሀመድ ናቸው።