ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጋሞና ወላይታ ዞኖች 175 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጋሞና ወላይታ ዞኖች 175 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ
አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 30/2015(ኢዜአ):- ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጋሞና ወላይታ ዞኖች በተቀናጀ ገጠር ልማት 175ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ እንደገለጹት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 219 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል።
ከተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክቱ በዞኖቹ በሚገኙ 44 ቀበሌዎች እንደሚተገበርም አስታውቀዋል።
ድርጅቱ በዘላቂ የመሬት አጠቃቀም፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰው ሀብት ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድረግ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በተያያዘም በሁለቱም ዞኖች 200 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ከ8 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን አፍልቶ በማልማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማህረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ 33 ጥልቅ ጉድጓዶችን እንደሚቆፍርና ምንጮችን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
እንዲሁም የሁለት ከፍተኛ 2ኛ ደረጃና ሁለት መለስተኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ አንደሚያከናውን ተጠሪው አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በጤና አጠባበቅ አገልግሎት፣ በገጠር ሴቶች ብድርና ቁጠባ መስኮች እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቲቆ ትላንቴ በበኩላቸው ድርጅቱ የሚያካሂደው የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮጀክት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃና በሌሎች ዘርፎች የገጠር ማህበረሰብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ማህረሰቡን በማስተባበር ድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡
ድርጅቱ መንግስትን ያልደረሰባቸውን የልማት ስራዎች በተለይም ገጠር የሚገኘውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ በጋሞ ዞን የቦረዳ ወረዳ ዞንጋ ዋጫ ቀበሌ አርሶ አደር ማራቃ ማዶ ናቸው።
ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ባለፉት 41 ዓመታት ከ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአካባቢ ጥበቃ፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሰው ሀብት ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ከ6 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።