የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2015 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች እውቅና ሰጠ። 

በመርሃ-ግብሩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንዲሁም የተለያዩ የጉዞ ወኪል እና የአስጎብኚ ድርጅቶች ኃላፊዎች ታድመዋል።


 

የእውቅና መርሃ ግብሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በዋናነት የቱሪዝም ዘርፍን ማነቃቃት ላይ ዓላማ ያደረገ ሲሆን፤ በስምንት ዘርፍ ለታጩ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል።

በዚህም ከፍተኛ ሽያጭ ላስመዘገቡ፣ ታማኝነታቸውን በተግባር ላሳዩ እንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ላይ የተሻለ ስራ ላከናወኑ ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል፡፡


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርትን ከማቀላጠፍ ባሻገር  ለቱሪዝም እድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ደግሞ የጉዞ ወኪሎች እና የአስጎብኚ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም