አየር መንገዱ የሰለጠነ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ የሰለጠነ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሰለጠኑ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በረዥምና በአጭር ጊዜ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 551 የአቪዬሽን ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።
ባለሙያዎቹ የተመረቁት በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ አስተናጋጅነት፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በንግድና በሆቴል ዘርፍ ነው።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተመራቂ ተማሪዎች ወላጆች ታድመዋል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሰው ኃይል ግንባታ በአየር መንገዱ ራዕይና ስትራቴጂ ውስጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዚህም በዛሬው ዕለት እያስመረቅናቸው ያሉት የአውሮፕላን አብራሪዎችና ሌሎች ባለሙያዎች አየር መንገዱ ግቡን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛሉ ነው ያሉት።
አየር መንገዱ በተያዘው በጀት ዓመት 22 በመቶ ለማደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚሁ ስኬት ደግሞ የሰው ኃይል ማብቃት ላይ መሥራት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሰለጠኑ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ካሴ ይማም በበኩላቸው የአቪዬሽን አካዳሚው ለአየር መንገዱ እድገት የጀርባ አጥንት ሆኖ ሲያግዝ ቆይቷል ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቁ የመስኩ ባለሙያዎችም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
በዛሬው እለት በአውሮፕላን አብራሪነት የተመረቁ ተማሪዎች በበኩላቸው በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ ሙያውን በብቃት እንዲወጡ የአቪዬሽን ዩንቨርሲቲው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ለኢዜአ ጠቁመዋል።
ባገኙት የሙያ ብቃት አየር መንገዱን በትጋት በማገልገል በአፍሪካ የያዘውን ሥመ ገናናነትና የመሪውን ድርሻ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡም ግልጸዋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1956 ጀምሮ በአቪዬሽን አካዳሚነት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ሲያሰለጥን ቆይቶ በቅርቡ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ማደጉ ይታወሳል።