ቀጥታ፡

የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረገ የአደጋ ምላሽ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው--ኮሚሽኑ

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረገ የአደጋ ምላሽ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል እና የክልል አካላት የተሳተፉበትና የቤተሰብ የኢኮኖሚ ሁኔታ ልየታ ላይ ያተኮረ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ እየተሰጠ ነው።

በዚህ ወቅት በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ታዬ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በህብረተሰብ የአኗኗር ዘይቤ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ወሳኝ ነው።

በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በዓመት ሁሉት ጊዜ በበልግና በመኸር ወቅት የእያንዳንዱን የህብረተሰብ ክፍል የአኗኗር ዘይቤን በአምስት መስፈርቶች ከፍሎ በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ እንደሚሰበስብ ጠቁመዋል።

የመረጃ አሰባሰቡ ደሀ፣ የደሀ ደሀ፣ መካከለኛ እና በእማውራዎች የሚመሩ ቤተሰቦች የሰብል ምርታቸው መቼ እንደጠፋ እንዲሁም በአካባቢው ገዥ የሆነው የአዝመራ ወቅት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ነው። 

በእዚህም የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረገ የአደጋ ምላሽ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ታዬ ያስታወቁት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ዜጎች በተምች፣ በጎርፍና በሌሎች ምክንያቶች የእንስሳት ሀብታቸው ጭምር ሊጎዳ ስለሚችል የአደጋ ምላሽ ስርአቱ ይህንን ጭምር በማጥናት ዝግጅት የሚደረግበት ነው።

በጥናት የተለዩት ሁሉ ተረጂ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከድጋፍ ባሻገር ህብረተሰቡ የትኛውን ሀብቱን ቢሸጥ ችግሩን ሊወጣ ይችላል በሚል መፍትሄ እንደሚጠቆምም አመልክተዋል።

እንዲሁም የሚዘረጋው የአደጋ ምላሽ ሥርዓት ለተጎጂው ምን ድጋፍ ቢደረግለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ሊቋቋምና ወደ ቀድሞ ቁመናው ሊመለስ ይችላል የሚለውን የሚመልስ ይሆናል።

ክፍተቱን ለመሙላት ከማህበረሰቡ እና በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች ድጋፍ ለማመቻቸት ጭምር እንደሚያስችልም አስታውቀዋል።

ስልጠናው በጥናት ላይ የተመሰረተ እና ትክክለኛ መረጃ የሚጠናቀርበትን ስልትና ክህሎት በማስጨበት ዘርፉን ለማሳለጥ ታስቦ መዘጋጀቱንም አቶ ታዬ አስታውቀዋል።

ይህም ከታች የሚመጣውን የተጋነነ የተረጂዎች ቁጥር በማስቀረት፣ የገበያ ግሽበትን ለማወቅና አርሶ አደሩ የሚያገኘውን ምርት ትክክለኛነት በማረጋገጥ ለክልሎች አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።


 

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር አገልግሎት የአደጋ ምላሽና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ዳኜ ስልጠናው ተጨማሪ እቅም እንደሆናቸው ገልጸዋል። 

የአኗኗር ዘይቤን መሰረት ያደረገ የመረጃ ማሰባሰቢያ ሥርዓት በተለያየ አደጋ የተጎዱትን ሰዎች ለይቶ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ይበልጥ የተጎዱትንና የጉዳታቸውን መጠን ለመለየት እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም ምን ዘዴ መከተል እንደሚገባ ከስልጠናው ክህሎት እንደቀሰሙ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከተረጂዎች ምልመላ ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመፍታትና ትክክለኛ የተጎዱትን ለመለየት የራሱ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል። 


 

የድሬዳዋ አስተዳደር የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን በሪ በበኩላቸው፣ "ስልጠናው ከአደጋ ምላሽ ጋር ተያይዞ ያለውን ተግዳሮት ለማቃለል አቅም ይፈጥራል" ብለዋል።

በተለይ አሁን ላይ ያለውን አማራጭ ሳይንሳዊ ዘዴ በውል በመረዳት የበለጠ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የድሃ ድሃውን ለይቶ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ የሚያነሳሳ ስልጠና ነው ሲሉም አክለዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ ስልጠና ላይ ከሁለት ከተማ አስተዳደሮችና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም