ቀጥታ፡

የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት መመከት አስችሏል - አቶ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፦ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት መመከት ማስቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር "የአመራር ልህቀት በሳይበር ዘመን" በሚል መሪ ኃሳብ ተቋማትን ያሳተፈ አገራዊ ጉባኤ አካሂዷል።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ጉባኤው የተቋማት መሪዎች በሳይበር አውድ የአመራር ጥበብና ልምድ ላይ መመካከር የሚችሉበት ነው።

በቴክኖሎጂና ዲጂታል ዘመን ለአገር አቀፍ የተቋማት አመራር ጥበብ ልምድ ለመቀመር ግብዓት የሚሆን ኃሳብ የሚመነጭበት መድረክ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዓለም ላይ በርካታ የአመራር ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እንደ ሌሎች የሙያ ዘርፎች ሁሉ የአመራር ጥበብን በሥልጠና ብቻ ማብቃት አይቻልም ብለዋል።

በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ የአመራር እውቀትና ልምድ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት አልሄደም ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በተቋማት መሪዎች መካከል ያለው ውስን የእርስ በርስ ግንኙነት ዛሬም ለታሰበው የኢትዮጵያ ብልጽግና ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።

የተቋማት መሪዎች ሰራተኞችን ለመምራትና ለማነሳሳት አሁናዊ የሳይበር ዘመን ነባራዊ ሁኔታን የተረዳ የአመራር አቅም ማጎልበት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

እውቀትና ክህሎትን ማዘመን፣ ማብቃት፣ ለማወቅ ጉጉት ያለውና ፈቃደኛ መሆን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከደረሱ ዘርፈ ብዙ የሳይበር ጥቃቶች መካከል ከ96 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በተቋማት ቅንጅታዊ አመራር በብቃት መመከት ተችሏል ብለዋል።

በሳይበር ጥቃት "ዛሬ የተከላከልከው ለነገ ዋስትና አይሆንም" ያሉት አቶ ሰለሞን፤ መሪዎች የሚመሩትን ተቋም ደህንነት በየጊዜው ማረጋገጥና በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ዘመንን የዋጀ የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት በመፍጠር የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ የሀገር በቀል የአመራር ጥበብን ማጎልበት እንደሚገባም ነው ያነሱት።

መሪዎች ቴክኖሎጂ ባመጣው ለውጥ ውስጥ በማለፍ የሳይበር ጥቃትን መከላከልና መመከት የሚችሉበት አቅም መፍጠር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ዘመንን የሚመጥን የተቀናጀ የአመራር ጥበብን መፍጠር የሚያስችል መድረክ በማዘጋጀት አገራዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የአመራር ልህቀትን በተመለከተ የመነሻ ፅሑፍ ያቀረቡት አቶ ለማ ደገፋ በዲጂታል ዘመን አንድ መሪ ብቻውን ሊለውጥ የሚችለው ተቋም የለም ብለዋል፡፡

በአንድ ተቋም ውስጥ ያሉ አካላት ሁሉም መሪዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በግለሰቦች ብቻ የተንጠለጠለ የአመራር ሰጭነት ሚናን ወደ ቅንጅታዊ አመራር መቀየር ይገባል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ሀገር ያስቀጠሉ እንቁ የመሪነት ጥበባት እንደነበሩ አስታውሰው፤ ውጤታማ አመራር ለመስጠት የሳይበሩን ዘመን ታሳቢ ያደረገ በአንድነት የመምራትን ልምድ ማዳበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም