የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑ አገሪቱ በልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑ አገሪቱ በልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፦ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑ አገሪቱ በልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን ተናገሩ።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ አጋር ከሆኑ የልማት አጋሮች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን ሲደግፍ ቆይቷል።
ለአብነትም ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የግብርና ልማት፣ ትምህርት፣ ጤና እና ዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ሁነኛ አጋር ሆኖ የዘለቀ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከከፍተኛ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ የልማት ሥራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ከጉብኝቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በተለይም በዓለም ባንክ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሆነው በማየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዓለም ባንክ በአጋርነት ደረጃ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ባንኩ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጉብኝትና ባንኩ ኢትዮጵያን ለመደገፍ በቀጣይም እንደሚሰራ ማረጋገጡን አስመልክቶ ከኢኮኖሚ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ፤ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ባላት አስተዋጽዖ ትኩረት የሚሰጣት አገር መሆኗን አመላካች ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጥሮ የነበረው ኮሮናን ጨምሮ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት መቻሏ አገሪቱን ሳቢ ካደረጋት ምክንያት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ከኢኮኖሚ ባሻገር በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ያላት ስለመሆኑም ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዕቅድ የሚመራ በመሆኑ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች ያሉት ዶክተር ብርሃኑ ይህንም ዓለም ባንክ የሚያበረታታው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በአገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ መርሃ-ግብር እና የአሥር ዓመቱ መሪ ልማት ዕቅዶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
እነዚህ የልማት አጀንዳዎች የዓለም ባንክ ከያዛቸው መርሃ-ግብሮች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ብርሃኑ፤ ዓለም ባንክ ኢትዮጵያን በቁርጠኝነት እንዲደግፍ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
የልማት ኢኮኖሚ ምሁሩ ደረጀ ደጀኔ በበኩላቸው፤ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት አጋር በመሆን በርካታ ፕሮጀክቶችን ሲደግፍ መቆየቱን አመላክተዋል።
ባንኩ የሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች ለአገሪቱ እድገት መረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ ዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሥራት ምን ያህል ቦታ እንደሰጠው አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።