ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማቆየት ወሳኝ በመሆኑ በልማቱ እየተሳተፍን ነው---የባንኩ ሠራተኞች

ዲላ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ)፡- አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማቆየት ወሳኝ በመሆኑ በልማቱ እየተሳተፍን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲላ ዲስትሪክት ሠራተኞችና ሃላፊዎች ገለጹ።

የዲስትሪክቱ ሠራተኞችና አመራሮች በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ካራ ሶድት ቀበሌ ዛሬ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።  

በእዚሁ ጊዜ ሠራተኞቹና አመራሮቹ እንዳሉት የችግኝ ተከላ መርሀግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማቆየት መሰረት የሚጥል ነው።

በመሆኑም ችግኞችን ተክለው በመንከባከብ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት የበኩለቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲላ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አላሎ እንዳሉት፣ በአረንጓዴ አሻራ የሚተከለው ችግኝ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አለው።

በዛሬ እለትም የዲስትሪክቱ ሠራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ካራ ሶዲት ቀበሌ በመገኝት የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኙ ከ10 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞች መትከላቸውን አስረድተዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረጃ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል የተያዘው ዕቅድ አካል መሆኑን ጠቁመው፣ "የተተከሉ ችግኞች እንዲጽድቁ አስፈላጊው ክትትልና እንክብካቤ ይደረጋል ብለዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማቆየት መሰረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ተረፈ ደንበል የተባሉ የባንኩ ሠራተኛ ናቸው።

ባለፉት አራት ዓመታት በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች ከመሳተፍ ባለፈ የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማሳደግ ለአረንጓዴ ልማት ስኬት የበኩለቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ ልማት እንዲረጋገጥ የሚያደርጉትን አስተዋጾ እንደሚያጠናክሩም አቶ ተረፈ አረጋግጠዋል።

"የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በማሰብ በልማቱ እየተሳተፉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የባንኩ ሠራተኛ አቶ ብርሃኑ አብርሃም ናቸው። 

ለመጪው ትውልድ በአረንጓዴ የለማች አገር ለማውረስ መርሀግብሩ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሀኑ፣ በዛሬው እለትም ከ10 በላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ተናግረዋል። 

"አረንጓዴ አሻራ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያስተሳሰረና ከተባበርን ታሪክ መስራት እንደሚንችል ያሳየንበት ነው" ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ለፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱ አካባቢን ከመጠበቅና የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም አቶ ብርሀኑ ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም