የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015            

2161

                       የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015

            የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

መንግስት የህዝብን ሰላም፣ የሃገር ደህንነትን፤ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤

በአማራ ብሄራዊ ከልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ፤

ይህ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፤

የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ህግ እና ስርዓት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል

                                               ክፍል አንድ

                                            ጠቅላላ ድንጋጌ

1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅየሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015* ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል

2.ትርጓሜ

ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል፦

1) የሕግ አስከባሪ አካል ማለት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ የሚያሰማራቸው ሌሎች የፀጥታ አካላት ማለት ነው፤

2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ” ማለት ይህን አዋጅ ለማስፈፀም በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 መሰረት የተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አደረጃጀት ማለት ነው፤

3)ሕግ” ማለት የፌዴራል ሕገ መንግስት፣ እንደ አግባብነቱ በፌዴራል ወይም በክልል መንግስታት ህግ አውጪ ወይም ስልጣን ባለው ህግ አስፈፃሚ አካል የወጣ የክልል ሕገመንግስት፣ አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ማለት ነው፤

4) ሰውማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ማለት ነው::

5) በዚህ አዋጅ በወንድ አነጋገር የተገለፀው ሴትንም ይጨምራል።

3. የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር እንዲሁም በክልሉ አስተዳደር የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚወሰድ እርምጃን፣ በክልሉ ወይም በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ችግር የሚያባብስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ወይም ሁኔታን በሚመለከት እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛዉም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

ክፍል ሁለት

ስለ አስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ

4. የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ መቋቋም እና ሃላፊነት

1) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሟል።

2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ አባላት፣ መዋቅር እና አደረጃጀት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን ይሆናል።

3) የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ጠቅላይ ዕዙ ተጠሪነት ለኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል።

4) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ፤

       ሀ) አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነት ወስደው

           የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈፃሚ የሚያደርጉ ግብረ ሃይሎችን ወይም ኮሚቴዎችን

           ሊያቋቁም ይችላል፣

       ለ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 የተመለከቱ እርምጃዎችን በተመለከተ አስፈላጊውን ውሳኔ

           ያስተላልፋል፣ ያስፈፅማል፣

      ሐ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 የተመለከቱ የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎችን

           ያስከብራል፣

      መ) በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላትን በአንድ ዕዝ

           ሥር አድርጎ በላይነት ያስተባብራል፣ ይመራል፣

      ) ኃላፊነቱን ለመወጣት ሌሎች አስፈላጊ እና አግባብ የሆኑ ስልጣኖች ይኖሩታል።

ክፍል ሶስት

በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች

5. በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተከለከሉ ተግባራት

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የዚህን አዋጅ አላማ ለማሳካት አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፦

 1. የአደባባይ ስብሰባና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን የመከልከል፣
 2.  የሰዓት እላፊ የማወጅ፤ ለተወሰነ ጊዜ አንድ መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ እና እንዲቋረጥ ለማዘዝ፣
 3. ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ለማዘዝ፣
 4.  የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስን ለመከልከል፣
 5.  በሀገረ መንግስቱ እና በህገመንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣስ እና አፈፃፀሙን የማደናቀፍ ወንጀልን መፈፀሙ፣ መምከሩ ወይም ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ማናቸውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር በማድረግ ለማቆየት፣
 6. ወንጀል እንደተፈፀመባቸውን ወይም ሊፈፀምባቸው እንደሚችል የተጠረጠሩ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በየትኛዉም ጊዜ ማናቸውንም ስፍራ እና መጓጓዣ ለመበርበር፣
 7. መንግስታዊ እና ህዝባዊ ተቋማትና የመሰረተ ልማቶች ጥበቃ ሁኔታን ለመወሰን፤
 8. ማናቸውም ከዚህ አዋጅ አላማ በተፃረረ መልኩ እየተነቀሳቀሱ እንደሆነ የተጠረጠሩ የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ሌሎች አካላት አንዲዘጉ፣እንዲቋረጡ፡ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወይም እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ ለማዘዝ፥
 9.  ማንኛዉም አገልግሎት መስጫ ተቋም እንዳይዘጋ እና ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማዘዝ፣
 10. ማንኛዉም የህዝብ ትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪዎች እና ማጓጓዣ እቃዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማዘዝ፣
 11. የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም፣ ማደራጀት ወይም የአስተዳደር እና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች አርምጃዎችን የመውሰድ፣
 12. የህዝብን ሰላም፣ የሃገር ደህንነትን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን የመዉሰድ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ትእዛዝ የመስጠት ስልጣን አለዉ፡፡

6. የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች

 1. ማንኛውም ሰው ይሆንን አዋጅ፣ በአዋጁ መሰረት የሚወጡ መመሪያዎችን የሚሰጡ ትዕዛዞች እና የሚተላለፉ ውሳኔዎችን የመተግበር እና የማክበር ግዴታ አለበት።

 1. የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና በክልሉ የአመጽ እንቅስቃሴን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር፣ እንዲሁም የፀጥታ መደፍረሱን የሚያባብስ ንግግር፣ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ቅስቀሳ በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት የተከለከለ ነው።

 1. በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለታጣቂ ቡድኖች የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።

4) ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።

5) ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፡፡

 6) ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የስራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ነው።

7) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፤ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

7. ተመጣጣኝ ሀይል ስለመጠቀም እና የማይታገዱ መብቶች

 1. የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ለማስፈፀም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሕግ አስከባሪ አካላት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ መመሪያ ለመስጠት ይችላል።
 2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎችም፤ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 93(4)() መሰረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን እና መብቶችን፣ እንዲሁም የተመጣጣኝነትን እና የአስፈላጊነት መርሆዎችን ማክበር ይኖርበታል።

ክፍል አራት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

 8. ተፈፃሚነታቸው የታገዱ ሕጎች

1)  በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እሲኪጠናቀቅ ድረስ በዚህ አዋጅ ንዑስ አንቀጽ 9 ከተገለፀው አግባብ ውጪ የትኛውም የዳኝነት አካል ስልጣን አይኖረውም።

2) በቪዬና ኮንቬንሽን፣ በሌሎች የአለም አቀፍ ስምምነቶች እና ደንቦች እውቅና የተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ መብቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈፃሚነታቸው ታግዶ ይቆያል:

9. የወንጀል ተጠያቂነት

1) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደ ጥፋቱ ክብደት እስከ አስር አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

2) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።

3 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁ እና በአዋጁ ማዕቀፍ የሚወጡ ደንብ እና መመሪያ ጥሰቶች የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም በኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 9(2) መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብ ይችላል።

4) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የሚመጣ የወንጀል ተጠያቂነትን አስመልክቶ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ መደበኛ የወንጀል ስነ ሥርዓት ድንጋጌዎችም ተፈፃሚነት አይኖራቸውም።

5) የፀጥታ ሁኔታው የመደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማያስችልበት ሁኔታ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ከዚህ አዋጅ ጥሰት ጋር ተያያዥ የሆኑ የወንጀል ጉዳዮችን አስመልክቶ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እና የፍትህ አካላት መደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላትን ተክተው እንዲሰሩ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሊወስን ይችላል።

10. ደንብ እና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን

1) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሃገርን ሰላምና ህልውና፣ የህዝብን ደህንነት፣ ህግ እና ሥርዓትን ለማስከበር በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93(4)() መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን ይኖረዋል።

2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በአዋጁ፣ ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት በሚወጡ ደንቦች የተሰጠውን ስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ እና ሃላፊነቱን ለመወጣት አስፈላጊ መመሪያዎችን ያወጣል።

3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሚወጡ መመሪያዎች ተፈጻሚ ከመደረጋቸው በፊት ለሕዝብ በስፋት ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ እንዲተዋወቁ መደረግ ይኖርበታል።

11. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

1) ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የፀና ይሆናል።

2) የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም