ቀጥታ፡

በፆመ-ፍልሰታ ምዕመናን ስለ ሰላምና ፍቅር እንዲማፀኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ጥሪ አቀረቡ  

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015(ኢዜአ)፦ በፆመ-ፍልሰታ ምዕመናን በተመስጦና በንስሐ ሕይወት ስለ ሰላምና ፍቅር እንዲማፀኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ጠየቁ።

አቡነ ማቲያስ የፆመ-ፍልሰታ መግቢያን አስመልክተው ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ፆመ-ፍልሰታ በፍቅር ለፍቅር የተፈጸመ ነው።

"የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረትና ጣሪያ፣ ወለልና ግድግዳ በፍቅርና በፍቅር ብቻ የተገነባ ነው፤ ፍቅር እግዚአብሔር ዓለምን ያዳነበት መድኃኒት ነው" ብለዋል። 

"ፍቅር የጥላቻና የመለያየት ግንብን ንዶ ይቅርታንና አንድነትን የሚገነባ ጠንካራ ዓለት ነው፤ ፍቅር መጽናናትንና ደስታን የሚያፈራ ጣፋጭ ተክል ነው፤ በፍቅር ለፍቅር የሚደረግ ሁሉ ፍስሐን እንጂ ጸጸትን አያስከትልም " ሲሉም ተናግረዋል። 

በመሆኑም ሕዝበ-ክርስቲያኑ በፆመ-ፍልሰታ በተመስጦና በንስሐ ሕይወት ስለ ሰላምና ፍቅር እንዲማፀኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፆሙ ወቅት ምዕመናን ስለ ሰላምና ፍቅር እየተማፀኑ ካላቸው በረከት ለተራቡትና ለተፈናቀሉት እንዲለግሱም አቡነ ማቲያስ ጠይቀዋል። 

በሌላ በኩል የሚፈጠሩ ችግሮችን በርካታ ጥፋቶችን የሚያስከትሉ መሆኑን ገልጸው ችግሮች ሲፈጠሩ በሥርዓትና በእርቅ መፍታት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም