የምክር ቤቱ ጉባዔ ሁለቱ ክልሎች የሚመሩበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በማጽደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱ ጉባዔ ሁለቱ ክልሎች የሚመሩበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በማጽደቅ ተጠናቀቀ
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 29 / 2015 (ኢዜአ)፡- የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ በነባሩ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል የሚኖሩ አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመሩበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ።
ከአዲሱ ክልል ጋር የሥልጣን ርክክብም ተደርጓል።
በሀዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ በተጠናቀቀው ሥነ- ሥርዓት ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኑሪዬ ሱሌ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርበዋል።
አቶ ኑሪዬ ለምክር ቤቱ አባላት የውሳኔ ሀሳቡን በንባብ ባቀረቡበት ወቅት ከገለጿቸው ውስጥ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልና የጋራ ክልል ለመመስረት በህዝበ ውሳኔ ድምፅ ባረጋገጡት ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በሚመሠረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል የሚኖረውን የንብረትና ዕዳ ክፍፍል ይገኙበታል።
እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮችን ፣የፍትሀዊነት ፣ የመልካም ግንኙነትና አብሮነት መርህን በጠበቀ መልኩ ለመምራት የቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሰው ኃይል ስምሪትና ድልድልን፣ የሰራተኞችን መሠረታዊ መብትና ጥቅሞች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለመምራት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ መሆኑ አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ ውይይት ካደረገበት በኋላ ውሳኔ ቁጥር 16/2015 ሆኖ አጽድቋል ።
በመጨረሻም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ ስድስት ዞኖችና አምስቱ ልዩ ወረዳዎችን ላሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥልጣን ርክክብ ካደረጉ በኋላ ጉባዔው ተጠናቋል ።