የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ አደረገ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015(ኢዜአ)፦ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ አድርጓል።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሃዋሳ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ አዲስ የሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጋር የስልጣን ርክክብ አድርጓል።
ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር ይተዳደሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ ባሳለፈው መሰረት ነው ዛሬ የስልጣን ርክክብ ለማድረግ የበቃው።
''የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል'' በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዴኦ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በኧሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ በጉባኤው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ መምከሩን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።