በጸጥታ ዘርፍ የተጀመረው ብቁ የሰው ኃይልን የማፍራትና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካዔል - ኢዜአ አማርኛ
በጸጥታ ዘርፍ የተጀመረው ብቁ የሰው ኃይልን የማፍራትና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካዔል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ)፡- በጸጥታ ዘርፍ የተጀመረው ብቁ የሰው ኃይልን የማፍራትና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ሊቀ-መንበር ደመላሽ ገብረሚካዔል ገለጹ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለ23ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን እጩ የፖሊስ መኮንኖችን አስመርቋል።
በምረቃ መርኃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቁት እጩ መኮንኖች ለስምንት ወራት ፖሊሳዊ ትምህርቶችን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካዔል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ከለውጡ ወዲህ ለጸጥታና ለደህንነት ሥራው በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አመርቂ ውጤት ታይቷል።
ለዚህ ደግሞ ዘርፉን በሠለጠነ የሰው ሃይል እንዲመራና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ የወንጀል አዝማሚያዎች እንዲከሽፉና ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተጀመረው ብቁ የሰው ኃይልን የማፍራትና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ፣ የኢትዮጵያ መዲናና የአለም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫ ማዕከል በመሆኗ ሰላሟን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የግድ ነው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ተመራቂዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ፍጹም በሆነ ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።