የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአብራሪነት፣ በአውሮፕላን ቴክኒሺያንነት፣ በበረራ አስተናጋጅነትና በማርኬቲንግ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአብራሪነት፣ በአውሮፕላን ቴክኒሺያንነት፣ በበረራ አስተናጋጅነትና በማርኬቲንግ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአብራሪነት፣ በአውሮፕላን ቴክኒሺያንነት፣ በበረራ አስተናጋጅነትና በማርኬቲንግ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 551 ባለሙያዎች አስመረቀ።
በመርኃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም፣ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተመራቂ ተማሪ ወላጆች ታድመዋል።
የአየር መንገዱ ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሰው ኃይል ግንባታ በአየር መንገዱ ራዕይና ስትራቴጂ ውስጥ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዚህም በዛሬው ዕለት እያስመረቅናቸው ያሉት የአውሮፕላን አብራሪዎችና ሌሎችም ባለሙያዎች አየር መንገዱ ግቡን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት።
በቀጣይም አየር መንገዱ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሰለጠነ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማፍራት የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1956 ጀምሮ በአቪዬሽን አካዳሚነት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ሲያሰለጥን ቆይቷል፤ በቅርቡም ወደ ዩኒቨርሲቲነት ማደጉ ይታወሳል።