የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ለአገር ሰላም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል- ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ለአገር ሰላም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል- ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ለአገር ሰላም ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ለአገራዊ ምክክሩ በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ጋር የቅድመ እና የዝግጅት ምዕራፍ የተሳታፊ ልየታ ሂደትን አስመልክቶ ትናንት በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መነሻ በማድረግ የዝግጅት ምዕራፉን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የዝግጅት ምዕራፉን ለማጠናቀቅም ተሳታፊዎችን በመለየት ከወረዳ እስከ ክልል የሚገኙ ተወካዮችን በማስመረጥ አገራዊ አጀንዳ በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
አጀንዳ የመሰብሰብ ተግባሩም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያካተት መሆኑን አንስተዋል።
በተሳታፊ ልየታ ሂደቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን የስምምነት ማዕቀፍ ወስደው ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም ነው ፕሮፌሰር መስፍን የተናገሩት።
አካታችና ገለልተኛ የተሳታፊ ልየታ እንዲኖር ድጋፍ በማድረግ ለሂደቱ ተዓማኒነት እገዛ እደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በሐረር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር የውይይትና የተሳታፊ ልየታ ማከናወኑንም ነው የገለጹት።
በክልሎች በተካሄዱ ውይይቶች ላይም የሚስተዋሉ የሰላምና ደህንነት ስጋቶች ለምክክር ሂደቱ እንቅፋት ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ማስቆም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው መግለጻቸውንም አንስተዋል።
በዚሁ መነሻነትም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የውይይት አጀንዳ ካሉም ለምክክር ዝግጁ በማድረግ ግጭቶችን ማስቆም የሚያስችል ምክክር እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንም አመልክተዋል።
ከ50 በላይ ከሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ውይይትም ሃሳባቸውን ያለ ገደብ በማንጸባረቅ ለምክክር ሂደቱ ስኬት በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ እንዲያደርጉ ታስቦ ተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
"ለግጭት መነሻ፤ ለሰላምም መፍትሔ" የሚሆኑት የፖለቲካ ልሂቃኑ መሆናቸውን ሕብረሰተቡ በተለያየ አጋጣሚ እያነሳ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት።
በዚሁ መነሻነትም በፖለቲካ የተደራጀ አካል ተወዳዳሪ የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር የአስተዳደር ስርዓትን ለመረከብ ሰላማዊ አገር እንዲሚያስፈልግ መገንዘብ ይኖርበታል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን በምክክር መርህ ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ለሕዝቦች ሰላም መሻትና መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ፤ ኮሚሽኑ የአገርን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እያካሄደ የሚገኘውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምክክር ሂደቱ ዋነኛ ባለድርሻ አካል በመሆናቸው ለስኬቱ ገንቢ ሚና በመጫወት ጠንካራ ብሔራዊ መስተጋብር ያላት አገር መፍጠር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች የፖለቲካ ሊሂቃን ተነጋግረው መፍትሄ ባለመስጠቱ የሚፈጠሩ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነትም የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና ተሳታፊዎች የራሳቸውን ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸውም ነው ሰብሳቢው ያስገነዘቡት።
ምክክር የፖለቲካ ሂደት በመሆኑ በፖለቲካ ሊሂቃን መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት መሆኑን መገንዘብም ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ሹምዬ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ፓርቲያቸው ግፊት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ከዝግጅት ምዕራፍ እስከ ተሳታፊ ልየታ ድረስ የሄደበት ርቀት በጎ ጅምር ቢሆንም ከተሰጠው የሶስት ዓመት ጊዜ አንጻር ግን ቀሪ ስራ እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
በሂደቱም ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ፈተናዎችንና ችግሮችን በመሻገር ለዜጎች ምቹ፤ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረባት አገር እንድትሆን ገንቢ ሚናችን እንወጣለን ብለዋል።
የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አህመድ አብዱ ሃጂ፤ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ለመስጠት አገራዊ ምክክር አድርጎ ከመግባባት መድረስ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬትም የሚችሉትን ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።