በሳይበር ዘመን የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት መፍጠር የሚያስችል አገር በቀል የአመራር ጥበብ ለማጎልበት እየተሰራ ነው - የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በሳይበር ዘመን የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት መፍጠር የሚያስችል አገር በቀል የአመራር ጥበብ ለማጎልበት እየተሰራ ነው - የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፡- በሳይበር ዘመን የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት መፍጠር የሚያስችል አገር በቀል የአመራር ጥበብ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር "የአመራር ልህቀት በሳይበር ዘመን" በሚል መሪ ኃሳብ ትምህርታዊ ጉባኤ እያካሄደ ነው።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጉባኤው የተቋማት መሪዎች በሳይበር አውድ የአመራር ጥበብና ልምድ ላይ መመካከር የሚችሉበት ነው።
በቴክኖሎጂና ዲጂታል ዘመን የተቋማት ለአገር አቀፍ አመራር ጥበብ ልምድ ለመቀመር ግብዓት የሚሆን ኃሳብ የሚመነጭበት መድረክ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በዓለም ላይ በርካታ የአመራር ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው እንደ ሌሎች የሙያ ዘርፎች ሁሉ የአመራር ጥበብን በሥልጠና ብቻ ማብቃት አይቻልም ብለዋል።
የተቋማት መሪዎች ሰራተኞችን ለመምራትና ለማነሳሳት አሁናዊ የሳይበር ዘመን ነባራዊ ሁኔታን የተረዳ የአመራር አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሳይበር ዘመን እውቀትና ክህሎትን ማዘመን፣ ማብቃት፣ ለማወቅ ጉጉት ያለውና ፈቃደኛ መሆን ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የሳይበር ዘመንን የዋጀ የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት በመፍጠር የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ የሀገር በቀል የአመራር ጥበብን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
መሪዎች ቴክኖሎጂ ባመጣው ለውጥ ውስጥ በማለፍ የሳይበር ጥቃትን መከላከልና መመከት የሚችሉበት አቅም መፍጠር ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ የአመራር እውቀትና ልምድ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት አልሄደም ያሉት አቶ ሰለሞን የተቋማት መሪዎች ውስን የእርስ በርስ ግንኙነት ዛሬም ለታሰበው የኢትዮጵያ ብልጽግና ፈተና መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የሳይበር ዘመንን የሚመጥን የተቀናጀ የአመራር ጥበብን መፍጠር የሚያስችል መድረክ በማዘጋጀት ተቋሙ አገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።