ቀጥታ፡

በተቋማት ውስጥ የህጻናት ማቆያ መኖር እናቶች ለልጆቻቸው በጊዜው ጡት እንዲያጠቡና እንዲንከባከቡ እድል የፈጠረ መሆኑን እናቶች ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015 (ኢዜአ) ፦ በተቋማት ውስጥ የህጻናት ማቆያ መኖር እናቶች ለልጆቻቸው በጊዜው ጡት እንዲያጠቡና እንዲንከባከቡ እድል የፈጠረ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ጡት የሚያጠቡ የቢሮ ሰራተኛ እናቶች ገለጹ።

የጡት ማጥባት ሳምንት በአገራችን “ለጡት ማጥባት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እንደግፍ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል። 

ጨቅላ ህፃናት ከተወለዱ ጀምሮ ቢያንስ ለተከታታይ ስድስት ወራት የጡት መጥባት እንደሚኖርባቸው የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህም የእናት ጡት ወተት ለህፃናቱ ጤና ተስማሚ የሆኑ ሁሉንም ንጥረ ነገሮች አካቶ እንደያዘም ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

ከጡት ማጥባት ሳምንት ጋር ተያይዞ ኢዜአ በተለያዩ ተቋማት በመዘዋወር የእናት ጡት ወተት ለልጆች የሚኖረውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ጡት የሚያጠቡ ሠራተኛ እናቶችን አነጋግሯል።

ወይዘሮ ማስተዋል ደባስ፤ በምትሰራበት መሥሪያ ቤት በተቋቋመው የህፃናት ማቆያ ሥፍራ በተቀመጠላት ጊዜ  በመጠቀም ልጇን እንደምታጠባ ገልፃ፤ የእናት ጡት ወተት የሚጠቡ ህፃናት በሽታን በመከላከል በኩል ጡት ከማይጠቡ ህፃናት የተሻሉ መሆናቸውን ገልጻለች።

በሥራ ቦታ ላይ ጊዜ በመስጠት ማጥባት እንደሚያስፈልግ የምትናገረው ወይዘሮ ጠየቁ ሙጬ በበኩሏ፤ ልጇ ጡት በመጥባቱ ከሚያገኘው ጥቅም ባሻገር እሷም ተጠቃሚ መሆኗን ነው የተናገረችው። 

ሌላዋ እናት ወይዘሮ ወጋየሁ አለኸኝ፤ በሥራ ቦታ የማያጠቡ እናቶች ጡት በማጥባት የሚገኘውን ጥቅም በማሰብ ህፃናት ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ መክራለች።

ወይዘሮ አቡሸት ንጉሴ የምትሰራበት ተቋም የህፃናት ማቆያ ሥፍራ በማቋቋሙ፤ ሙሉ ሃሳቧን ሥራዋ ላይ በማድረግ እና በቅርበት ልጇን ለማጥባት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላት ተጠቃሚ እንዳደረጋት ገልጻለች።

በምትሰራበት ተቋም በቀን ሦስት ጊዜ ልጇን እንደምታጠባ የምትናገረው ወይዘሮ ብርቱካን ደሱ በበኩሏ፤ በቅርበት ልጇን እያጠባች በሥራዋም ውጤታማ መሆን እንደቻለች ነው የምትናገረው። 

ጡት በማጥባት ህፃናት የእናትነት ፍቅር ሊያገኙ እንደሚችሉም ወይዘሮ ብርቱካን ከልምዷ አካፍላለች።

ጡት በማጥባቷ የመጀመሪያ ልጇ ንቁና በቀላሉ በበሽታ የማይጠቃ መሆኑን የምትናገረው ደግሞ ወይዘሮ እማዋይሽ ሽፈራው፤ በሥራ ቦታ በማጥባቷ የህፃናት ጤንነት በመጠበቅ ለተሻለ የአካልና የአዕምሮ ዕድገት ልጇን እያዘጋጀችው እንደሆነ ነው የተናገረችው።

እነዚህ እናቶች የእናት ጡት ወተት ለህፃናቱ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ከወዲሁ በመረዳት በተለያየ መስክ የተሰማሩ እናቶች ህፃናት ልጆቻቸውን ጡት እንዲያጠቡ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ሠራተኛ እናቶች ጡት እንዲያጠቡ መደገፍ እንደሚያስፈልግ በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ዳርሰኒ በጡት ማጥባት ሳምንት መርሃ-ግብር መክፈቻ ላይ መግለጻቸው ይታወሳል።

የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም