ህብረተሰቡ የበጎ ፈቃደኝነት የደም ልገሳን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የበጎ ፈቃደኝነት የደም ልገሳን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ፤ ሀምሌ 29/2015 (ኢዜአ)፡- ህብረተሰቡ የበጎ ፈቃደኝነት የደም ልገሳን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።
በመላው ዓለም ላይ በርካታ ዜጎች መዳን እየቻሉ በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
በኢትዮጵያም የኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የአቅርቦት መጠኑ ምን እንደሚመስል ኢዜአ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጤናዬ ደምሴን ጠይቋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጤናዬ እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
ለአብነትም በ2007 ዓ.ም መሰብሰብ የተቻለው የደም መጠን 56 ሺህ ዩኒት ብቻ እንደነበር በማስታወስ በ2015 ደግሞ 350 ሺህ በላይ ዩኒት መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ነገር ግን ከሚፈለገው አንጻር ሲታይ ገና ብዙ የሚቀር በመሆኑ ጥቂት የማይባሉ ወገኖች አሁንም በደም እጦት ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን አመላክተዋል።
በወሊድ እና በድህረ ወሊድ ከፍተኛ ደም የሚፈሳቸው እናቶች፣ ህጻናትና የካንሰር ህመምተኞች የችግሩ ግንባር ቀደም ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ የደም እጥረት እንዳያጋጥም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የደም ማሰባሰቢያ ጣቢያ በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሐ ግብር እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 108 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ማቀዱንም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ የጠቆሙት።
በመሆኑም ዜጎች በሁሉም ክልሎች በተዘጋጁ ጣቢያዎች በመገኘት በበጎ ፈቃደኝነት ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጁ የደም ልገሳ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ ቅኝት በማድረግ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን አነጋግሯል።
ለ21ኛ ጊዜ ደም መለገሱን የተናገረው ወጣት ካሳሁን ፍቃዱ ደም መለገስ ምንም አይነት የጎንዮሽ የጤና ጉዳት እንደሌለውና የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ደም ስትለግስ ያገኘናት ወጣት ማህደር ገዛኸኝ በበኩሏ፣ በወሊድም ሆነ በሌላ ምክንያት ደም የሚፈልጉ ሰዎችን ህይወት ለማዳን እድሉን በማግኘቷ መደሰቷን ገልጻለች።
ደም መለገስ ሰዎችን ከህመማቸው ከመፈወስና ከሞት ከማዳን ባሻገር ለደም ለጋሾችም ጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተገንዝቢያለሁ ያሉት ደግሞ አቶ ሁሴን ቶፊቅ ናቸው፡፡