ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሎዶን ዩናይትድ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 29/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታውን ዛሬ ከሎዶን ዩናይትድ ጋር ያደርጋል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የሚመሩት ዋልያዎቹ የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ አሜሪካ ይገኛል።

በመጀመሪያው ጨዋታው የጉያና ብሔራዊ ቡድንን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ቡድኑ ሁለተኛ ጨዋታውን በቨርጂኒያ ግዛት በሚገኘው ሴግራ ፊልድ ስታዲየም መቀመጫውን በግዛቱ ካደረገው ሎዶን ዩናይትድ ጋር ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።

ሎዶን ዩናይትድ በአሜሪካ የሊግ መዋቅር በሁለተኛው እርከን ላይ (UCL Championship) የሚወዳደር ሲሆን በዲሲ ዩናይትድ መጋቢ ቡድንነት እ.አ.አ በ2018 ከተመሰረተ በኋላ በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ በመቋቋም በአሜሪካ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። 

ክለቡ 5 ሺህ  ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሴግራ ፊልድ ስታዲየም ባለቤት ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ ቆይታው ለልምምድና ጨዋታዎች እየተጠቀመበት ይገኛል።

የዛሬው ጨዋታ ዋልያዎቹ ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ቢያዝም አዘጋጁ ተቋም የጨዋታው ትኬት በበቂ ሁኔታ እንዳልተሸጠ በመግለጽ ጨዋታው እንዲሰረዝ መጠየቁን ተከትሎ በአትላንታው ጨዋታ ምትክ የተዘጋጀ የወዳጅነት ጨዋታ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ለብሔራዊ ቡድን ተጠርተው ወደ ስፍራው ካመሩት ተጫዋቾች በተጨማሪ ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ ተደርጎላቸው በአሜሪካ ቡድኑን የተቀላቀሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ግብ ጠባቂ ዳንኤል ንጉሴ እና የመስመር ተጫዋቹ ማርከስ ቬላዶ ፀጋዬ በዛሬው ጨዋታ ላይ የመጫወት እድል ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያከናውን ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም