ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዝ ተችሏል - የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤  ሐምሌ 28 /2015 (ኢዜአ) ፡- በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት  ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዝ መቻሉን  የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ የምግብ ዘይት  እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በኮሚሽኑ የጉምሩክ ህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ለኢዜአ እንደተናገሩት በኮትሮባንድ ወንጀል የሚሳተፉ ግለሰቦች ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ወንጀል የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻሉን  ነው የተናገረት፡፡

በዚህም 1 ሺህ 339 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስራ በማዋል ለህግ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከተያዙት ንብረቶች መካከል ለማህበረሰብ ጤና አደገኛ የሆኑትን በመቅበርና በማቃጠል በአግባቡ የማስወገድ ስራ መከናወኑንም አክለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት የቀረጥና የጉምሩክ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ደንበኞች ባሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ በየትኛወም ወደብ ላይ ለሚገኙ እቃዎች ደንበኞች ባሉበት ስፋራ ሆነው የሚከፍሉበት አሰራር በቴሌ ብር አማካኝነት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

አስፈላጊ አገልግሎቶች በተቀመጠው መስፈርት እየተሰጠ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ታላላቅ ድርጅቶች በስፋት በሚገኙበት ቦታ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ አሳውቀዋል፡፡

በተመሳሳይም በሌሎች የንግድ ማዕከላት በሚገኙበት ቅርጫፎች እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም