ማዜ ብሔራዊ ፓርክን ለማልማት የሚውል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማዜ ብሔራዊ ፓርክን ለማልማት የሚውል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2015 (ኢዜአ) ፦የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ማዜ ብሔራዊ ፓርክን ለማልማት የሚውል የ5 ሚሊዮን ዩሮ ሥምምነት ከሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ጋር ተፈራረመ።
የገንዘብ ድጋፍ ሥምምነቱንም የሃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮማን ተስፋዬና የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ሶኒያ ሊኦሬት ተፈራርመዋል።
በሥምምነቱ መሰረት ፓርኩን የማልማት ሂደት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል።
የማዜ ብሔራዊ ፓርክ መልማት ለአገር ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ጎን ለጎን በፓርኩ አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።
የሥምምነቱ መፈረም የሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዝሃ ህይወትን ለመንከባከብ የያዘውን ዕቅድ የሚደግፍ መሆኑም ተገልጿል።
የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በ1997 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ202 ስኬዌር ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለውም ይነገራል።
ፓርኩ በደቡብ ክልል በጎፋ እና ጋሞ ዞን አምስት ወረዳዎች ይዋሰናል፤ ፓርኩ ማዜ የተሰኘውን መጠሪያ ስም ያገኘው ፓርኩን አቋርጦ ከሚፈስ ወንዝ ስለመሆኑም ይነገራል ።
በሥምምነት መርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።