በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ125 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮንትሮባንድ ጫት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ125 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮንትሮባንድ ጫት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 28/2015 (ኢዜአ)፦ በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ125 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ኮንትሮባንድ ጫት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተያዘ።
የተያዘው ጫት መነሻውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ አውሮፓ ሀገራት በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ መሆኑም ተመላክቷል።
መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት ይጓዝ የነበረ ኔዘርላንዳዊ ዜግነት ያለው የአንድ ተጓዥ 2 ሻንጣዎች ላይ በተደረገ ምርመራ መጠኑ 62 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የሆነ እርጥብ ጫት በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊያወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ወደ ለንደን የሚጓዝ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ የነበሩ 2 ሻንጣዎች በፍተሻ ወቅት መጠኑ 62 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም እርጥብ ጫት በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊያወጣ ሲል በቁጥጥር ውሏል።
በድምሩ 125 ነጥብ 15 ኪሎ ግራም የሚመዝን እርጥብ ጫት በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊያወጣ ሲል ሊያዝ የቻለው በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት የፍተሻ ባለሙያዎች ከጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ሰራተኞች እና ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በተደረገ ፍተሻ እና ጥብቅ ቁጥጥር ነው።
ሁለቱ ተጠርጣሪ የዉጭ ሀገር ዜጎች በአሁኑ ወቅት በህግ በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አግልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአደንዛዥ ዕፅን ጨምሮ ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራት በኢትዮጵያ አየር መንገድና ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዳይተላለፉ የሚያካሂደው ጠንካራ የመከላከልና የቁጥጥር ስራ አጠንክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።