ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 28/2015 (ኢዜአ) ፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የሰላም ሂደት፣ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት ትብብር እንዲሁም የጋራ ጥቅሞቻቸው በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ ደመቀ ለልዩ ልዑኳ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን ለማጽናት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደትና የመልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ስራዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ከዚህም አኳያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆን አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አጋሮች የመንግስትን አጠቃላይ ጥረቶች እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
ከሱዳን ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት አገር የሱዳን ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው በድርድር እና ውይይት ብቻ መሆኑን በጽኑ ታምናለች ነው ያሉት አቶ ደመቀ።
የሰላም ሂደቱ በባለቤትነት መመራት ያለበት በሱዳናውያን እንደሆነ ገልጸው የሰላም ጥረቶች በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አማራጭ ውስጥ ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ከሱዳን ጦርነቱን ሸሽተው የመጡ 70 ሺህ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ጠቁመው ለሰብአዊ እርዳታ ጥረቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲጸና እንዲሁም በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ገንቢ ሚና ለመወጣት አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን አመልክተዋል።