በኢትዮጵያ እሴት በመጨመር የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እሴት በመጨመር የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እሴት በመጨመር የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል "አንድ ተመራጭ ምርት በአንድ ሀገር" የተሰኘ የሁለት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በኢትዮጵያ የአመጋገብ ስርዓትን ለማሻሻል ጤፍን በልዩ ጥራት ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በጤፍ ምርት ላይ እሴት በመጨመር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2021 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሚቆየው የዓለም አቀፍ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የተመራጭ የግብርና ምርቶች ፕሮግራም አካል ነው።
የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙዲዚ እንዳሉት፣ የተመራጭ የግብርና ምርቶች መርሀ-ግብር አካል የሆነው የ"አንድ ተመራጭ ምርት በአንድ ሀገር" ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ጤፍ ምርታማነት ለማሳደግ የጎላ ሚና አለው።
ጤፍ የፕሮጀክቱ አካል እንዲሆን በኢትዮጵያ መንግስት የተመረጠ መሆኑን ገልጸው፣ ጤፍ ከግሉቲን ነፃ በመሆኑ በመላው ዓለም ተፈላጊ ምርት እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጤፍ ሚሊዮኖች አርሶ አደሮች የሚያመርቱትና የምግብ ዋስትናቸው መሰረት በመሆኑ ምርታማነቱን ማሻሻል ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል።
በጤፍ ምርት ላይ እሴት በመጨመር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሁሉንም አካላት ትብብር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።
የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት የአርሶ አደሩን የአመራረት ስልት በማሻሻል ቀጣይነት ያለው ምርታማነትንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ አማካሪ አብዱልሰመድ አብዶ፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሶስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በጤፍ ይሸፈናል ብለዋል።
ከ70 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉበትና በስፋት የሚመረት መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለምን 90 በመቶ ጤፍ የምታመርተው ኢትዮጵያ በአውሮፓ፣ አሜሪካና ኤዥያ ሀገራት ተፈላጊ ምርት ቢሆንም የማምረት አቅሟን ያክል እየተጠቀመችበት አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም ከዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይሄው ፕሮጀክት የጤፍን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።