ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚመረቱ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል - የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 28/2015 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ የሚመረቱ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ አሳሰቡ፡፡

የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናት እና ጌጣጌጥ አቅራቢዎች፣ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር የምስረታ በዓሉን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፣ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እና አለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና የማህበሩ አባላት በተገኙበት አክብሯል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት አመታት የከበሩ ማዕድናት ማህበር ባለመኖሩ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያክል ገቢ ተገኝቷል ማለት አይቻልም፡፡

በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ የከበሩ ማዕድናት እና ጌጣጌጥ አቅራቢዎች፣ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር መመስረት አስፈለጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በመድርኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ማህበሩ ትርጉም ባለው መልኩ በመስራትና ህጋዊ አሰራሮችን በመከተል የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም በኢትዮጵያ የሚመረቱ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ገልፀው፤ የዘርፉ ተዋናዮች በቅንጅት በመስራት የሀገርን ጥቅም በማስቀደም ሊሰሩ እንደሚገባ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም