ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2015 በጀት ዓመት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨቱን አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው የባንኩን አፈጻጸም በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ባንኩ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ተከታታይ ኪሳራ ሲያስመዘግብ ነበር ብለዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ግን የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ባንኩን ወደ ጤናማነት መመለስ መቻሉን አብራርተዋል።

ባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ስኬታማ መሆን መቻሉን አስረድተዋል።

የተበላሸ ብድር ምጣኔ 2010 ዓ.ም 43 ነጥብ 1 በመቶ ደርሶ ነበር ያሉት ዶክተር ዮሃንስ አሁን ላይ የተበላሸው ብድር መጠን ወደ 7 ነጥብ 1 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል።

ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወይም የኮርፖሬት ብድርን በተመለከተ በ2012 ዓ.ም 22 ነጥብ 8 በመቶ የተበላሸ ብድር እንደነበር አስታውሰው አሁን ወደ 3 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የተበላሸ ብድር በመቀነስ፣ ያሉትን ፕሮጀክቶች ጤናማነት በማሳደግ እና በማስተካከል የባንኩ ትርፋማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል።

ባንኩ በጀመራቸው አዳዲስ አሰራሮች ውጤት በማምጣቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን ተናግረዋል።

የባንኩን ካፒታል በአሁኑ ወቅት 38 ቢሊዮን ብር ደርሷል ያሉት ዶክተር ዮሃንስ፤ ይህም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ ትልቅ ካፒታል ያስመዘገበ ባንክ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።

ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት አኳያ ባንኩ ባለፈው ዓመት 22 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብድር ማጽደቁን ጠቁመው በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ 46 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን አስረድተዋል።

ብድሩ የፀደቀው በግብርና ዘርፍ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው እንዲሁም በማዕድን ዘርፎች ለተሰማሩ አካላት መሆኑን አክለዋል።

ባንኩ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማድረግ ላይ አበረታች ሥራዎች ማከናወኑን በመጥቀስ፤ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትም ካጸደቀው የብድር ገንዘብ ውስጥ 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩን ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም