የመደመር እሳቤ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ቁልፍ መሰረት እንደሚሆን ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ቁልፍ መሰረት እንደሚሆን ተገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ) ፦ የመደመር እሳቤ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ቁልፍ መሰረት የሚሆን ነው ሲሉ ኢዜአ ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ መድረክ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት “መደመር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር አዲሱ አረጋና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በመድረኩም የመደመር እሳቤ ከአገር በቀል እውቀቶች ጋር ያለው ትስስር፤ ለተቋማት ግንባታ ያለው ሚና፤ መደመርና ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የመደመር ቀጣይ እድሎችና ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የመደመር እሳቤ ለሰላም፣ ለልማት እንዲሁም ለብልጽግና መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ከተሳታፊዎች በርካታ ሃሳቦች ተነስተዋል።
መደመር በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አገር በቀል እሴቶችን በውስጡ የያዘ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተዋህዶ እንዴት መኖር እንዳለበትም ጭምር ያመላክታል ብለዋል፡፡
በተናጠል ያሉ ነገሮች ሲደመሩ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ውጤት እንደሚሰጡ በማንሳት፤ የማይደመሩ፣ የሚጋጩ የሚመስሉ ሁሉ ሲደመሩ አገርን የሚለውጡና አቅም የሚሆኑ ጉዳዮች ይሆናሉ ነው ያሉት።
የመደመር እሳቤ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት በማድረግ ለኢትዮጵያ መጻኢ ጉዞ ቁልፍ መሰረት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም በመደመር እሳቤዎች ወደ ህብረተሰቡ ደርሰው ምልዑ የሆነ ተቀባይነት እንዲያገኙ ምን መሰራት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥንትም በአንድነት ታሪክ በመስራት ይታወቃል ያሉት ተሳታፊዎቹ የጥንቱን ታሪክ ለማስቀጠል ከአሁናዊ ሀገራዊ አውድ አንጻር እንዴት መጓዝ እንደሚገባ መንገዱ ግልፅ ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
በሌላ መልኩም ተቋማትን ለተገልጋዮች ምቹ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የጠቆሙት።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ መደመር ለሁሉም ጥያቄዎች የመፍቻ ቁልፍ ያለው አገር በቀል እውቀት ነው ብለዋል፡፡
የህግ ምሁሩ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ በየማህበረሰቡ ያሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማሰባሰብ ወደ ጥቅም ለመቀየር የፖለቲካ ልሂቃን እና የሚመለካተቸው ሁሉ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ-ዓለም ዘርፍ ኃላፊ ዛዲግ አብርሃ፤ ኢትዮጵያውያን በረጅም ታሪካቸው አንድነታቸውን በማስጠበቅ ትልልቅ ታሪኮችን ያሥመዘገቡ መሆናቸውን አውስተዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች የሚፈቱት በአገራዊ ምክክር ነው ያሉት አቶ ዛዲግ፤ ለዚህ ውጤታማነትም ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ በበሉላቸው፤ ተቋማትን ለሰራተኞችና ለተገልጋዮች ምቹ የማድረግ ሂደቱን በማስፋት ባህል የሚሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይገባል ብለዋል፡፡
ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተመጣጠነ አመጋገብን ለማሻሻል እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ ናቸው፡፡