ቀጥታ፡

የኮንሶ ብሔር "አራራ" ባህላዊ የሸንጎ ስርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰራ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ

ካራት ፤ሐምሌ 27/2015 (ኢዜአ):- በኮንሶ ብሔር ለህብረተሰቡ አብሮነትና ሰላም አስተዋጾ ያለው "አራራ" የተሰኘው ባህላዊ የሸንጎ ስርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየሰራ መሆኑን የኮንሶ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የሸንጎ ስርአቱ ለማህበረሰቡ አብሮነትና ሰላም ካለው ጠቀሜታ ባለፈ በፍትህ ስርአት ላይ ጫና እንዳይፈጠር የራሱን አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኮንሶ ዞን አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሠራዊት ዲባባ እንዳሉት፣ ለነዋሪዎች የአብሮነትና የሰላም ዕሴት መጠናከር "አራራ" ባህላዊ የሸንጎ ስርዓት ተኪ የለሌው ሚና እየተጫወተ ነው።

ባህላዊ ስርአቱ በየትኛውም ሁኔታ የሚፈጠር አለመግባባት ያለቂም እና በቀል በዘላቂነት እንዲፈታ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ እርስ በርሱ ተዋዶና ተከባብሮ እንዲኖር በማስቻል በኩልም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

"ባህላዊ የሸንጎ ወይም የእርቅ ስርአቱ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገር የመጣው ለአንድ ወገን የማያዳላ፣ ምስክር የማይፈልግ፣ ከእርቅ በኋላም የሁለቱንም ወገኖች ግንኙነት የሚያጠናክርና ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የሚፈጥር በመሆኑ ነው።" ብለዋል።

በመሆኑም አራራ ባህላዊ የሸንጎ ስርአት ሳይበረዝ ለተተኪው ትውልድ እንዲሸጋጋርና ተሰንዶ እንዲቀመጥ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሠራዊት አስታውቀዋል።

አቶ ሠራዊት እንዳሉት ህላዊ ሸንጎው በፍትህ ስርአቱ ላይ ጫና እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡ በፍርድ ቤት ሙግት ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘቡን እንዳያባክን የሚያግዝ ነው።

ከሁሉም በላይ ሁለቱን ወገኖች ቅያሜ ውስጥ ሳይገቡ ቀጣይ ህይወታቸውን በሰላም እንዲመሩ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

በኮንሶ የጎሣ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው እንዳሉት የኮንሶ ብሔር “አራራ” የሸንጎ ስርአት ለህብረተሰቡ አብሮነት፣ ሰላምና ተከባብሮ መኖር የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው።

በኮንሶ ብሔር ከሚገኙ ዘጠኝ ጎሳዎች መካከል የትግሰይዳ ጎሣ መሪ አቶ ካፖሌ ገድሻ የእርቅ ስርአቱ በማህበረሰቡ መካከል ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲከሰቱ ለመፍታት የሚያስችል ነው።

የእርቅ ስርአቱን የሚያስፈጽሙት በአካባቢው የሚገኙ የጎሣ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ሲሆኑ የሚፈጸምበት ስፍራም “ሞራ” ወይም መሰብሰቢያ አደባባይ እንደሚባል ነው የገለጹት።

አቶ ካፓሌ እንዳሉት የአንድ ጎሣ አባል ጥፋት ቢፈጽም የተበዳይ ወገን ለጎሣ መሪው አቤቱታ ሲያቀርብ የጎሣ መሪው ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ግለሰቦችን ወደ “ሞራ አደባባይ” በመውሰድ ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታ ያደርጋሉ። 

አቶ ካፖሌ እንዳሉት በሞራ አደባባይ መዋሸት አይቻልም፤ የዋሸ አካልም መላው ቤተሰብ በሞት ይቀሰፋል ተብሎ ስለሚታመን ሁለቱም ወገኖች እውነቱን በመናገር ቂም ሳይዙ ይታረቃሉ።  

ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ኮራ ጋራ በበኩላቸው እንዳሉት በኮንሶ ዘጠኝ ጎሣዎች የአንድ አብራክ ልጆች በመሆናቸው ያለምንም ልዩነት በሰላም፣ በፍቅር፣ በመከባበርና መተባበር ለዘመናት ኖረዋል።

አንዳንዴ በጎሳዎች፣ በግለሰቦችና በባልና ሚስት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በ ”አራራ” የእርቅ ስርአት “ሞራ” አደባባይ ላይ ችግሩን በመፍታት ሰላም እንዲያወርድ ይደረጋል።

በሞራ አደባባይ አባቶችና የጎሣ መሪዎች ግጭት ከመፍታት በላይ በስነ-ምግባር የታነጸና አባቶችን የሚሰማ ትውልድ ለመፍጠር ታዳጊ ወጣቶችን ሰብስበው ምክርና ተግሳጽ እንደሚሰጡም አቶ ኮራ አስረድተዋል።

የሀገር ሽማግሌው እንዳሉት ባህላዊ የእርቅ ስርአቱ የእርስ በርስ ሰላምን በማጠናከር ነዋሪው ሥራው ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ ለልማት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። 

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ባህሉን ወርሶ እንዲያስቀጥል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም